ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነገ ፓርላማ ሊቀርቡ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነገ ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 በሚካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሊሰጡ ነው። ጥያቄዎቹ የፌዴራል መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ለፓርላማ ሪፖርት ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው በ2008 ዓ.ም የወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ይደነግጋል። ምክር ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ፤ በነገው ስብሰባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎች የመንግስታቸውን የዘንድሮ በጀት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የተመለከቱ እንደሚሆኑ ገልጿል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለት የፓርላማ አባላት፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንዲያቀርቡ የተነገራቸው የፌደራል መንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ሳይሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል። ጥያቄዎቻቸውን አስገብተው እንዲያጠናቅቁ ቀነ ገደብ የተሰጣቸው እስከ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መሆኑን የገለጹት የፓርላማ አባላቱ፤ ሆኖም ሪፖርቱ የተላከላቸው በበነጋታው መሆኑን አስረድተዋል።

የፓርላማ አባላቱ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ በተካሄደ የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥያቄዎች አቅርበው ዝርዝር ምላሽ ማግኘታቸው ይታወሳል። በዚሁ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት ውዝግብ ይገኝበታል። 

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት፤ ከትላንት በስቲያ በቱርክ አንካራ ያደረጉት ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። በቱርክ አመቻችነት ከተደረገው ከዚህ ውይይት መጠናቀቅ በኋላ፤ ሁለቱ ሀገራት በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ሁለተኛ ዙር ውይይት ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጿል።  

በነገው የፓርላማ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄዎች ከሚሰጡት ምላሽ በተጨማሪ የፌደራል መንግስት የ2017 በጀትን በተመለከተ የተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ያደምጣል። ይህን ተከትሎ ከሚደረግ ውይይት በኋላ በጀቱ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ለዕረፍት ለመበተን ሶስት ቀናት ብቻ የቀሩት ፓርላማው በነገው ስብሰባው፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅን ጨምሮ አራት አዋጆችን መርምሮ እንዲያጸድቅም በአጀንዳ ተይዞለታል። በተወካዮች ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የማጠቃለያ ሪፖርት ላይ የሚደረግ ውይይትም በነገ አጀንዳ ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)