በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ ውስጥ ካሉ ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ ከሚኒስትርነታቸው ተነስተው አማካሪ ተደረጉ። ለሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከካቢኔ አባልነታቸው ተሰናብተው፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል።
አቶ ቀጄላ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ካቢኔ የተቀላቀሉት፤ በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንድ አንጃ በመወከል ነበር። ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ፤ በመስከረም 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከተሾሙ 22 ሚኒስትሮች መካከል አቶ ቀጄላ አንዱ ነበሩ።
በዚህ ወቅት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትርነት ሹመት ካገኙት አቶ ቀጄላ በተጨማሪ፤ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቢኔ አባል ሆነዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር ሲሆኑ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ዶ/ር በለጠ ሞላ ደግሞ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ተሹመዋል።
አቶ ቀጄላ ከስልጣናቸው መነሳታቸው በተነገረበት በዛሬው ዕለት፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የ2016 በጀት ዓመት የዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም እና የመጪውን ዓመት እቅድ አስመልክቶ ውይይት ሲያደርጉ ነበር። ተሰናባቹን ሚኒስትር በመተካት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ናቸው።
ወ/ሮ ሸዊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። የብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑት ሸዊት ለፓርላማ የተመረጡት፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ወላይታ ዞን፣ ቦሎሶ ሶሬ ምርጫ ክልል ነው።
ሸዊት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ከመመረጣቸው አስቀድሞ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዝና ማረጋገጫ ባለስልጣን መስሪያ ቤትን በዋና ስራ አስኪያጅነት መርተዋል። አዲሷ ሚኒስትር በውጭ ቋንቋዎች ትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው።
በዛሬው ሹም ሽር እንደ እርሳቸው ሁሉ የሚኒስትርነት ስልጣን ያገኙት አቶ ካሳሁን ጎፌ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቶ ካሳሁንን የሾሟቸው፤ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በሚኒስትር ዴኤታነት ሲሰሩበት በቆዩት መስሪያ ቤት ነው። አቶ ካሳሁን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍን ሲመሩ ነበር የቆዩት።
ተሿሚው በትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትም በሚኒስትር ዲኤታነት ሰርተዋል። አቶ ካሳሁን ወደ ፌደራል መስሪያ ቤቶች ከመዘዋወራቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ባለስልጣንን በኃላፊነት መርተዋል። በአዳማ ከተማም በምክትል ከንቲባነት አገልግለዋል።
አቶ ካሳሁን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር። ይህንኑ በማስመልከት ባለፈው ሳምንት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “የእንኳን ደስ ያልዎት” ስነ ስርዓት አካሄዶላቸው ነበር። በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ዛሬ ከስልጣናቸው የተነሱት አቶ ገብረመስቀል “ትምህርት አቅም ይፈጥራል። በተፈጠረው አቅምም በተሻለ መልኩ ማገልገል ይጠበቃል” ሲሉ ተናግረው ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዛሬው ዕለት ያወጣው የሹመት መረጃ፤ አቶ ገብረመስቀል ከሚኒስትርነታቸው የተሰናበቱት ከሰኔ 26፤ 2016 ጀምሮ መሆኑን ቢገልጽም፤ ከቀናት አስቀድሞ ግን በክልል ደረጃ ሹመት ማግኘታቸው ተገልጾ ነበር። አቶ ገብረመስቀል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው መሾማቸው ይፋ የተደረገው ባለፈው አርብ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በዚሁ ዕለት ባወጣው አጭር መግለጫ፤ አቶ ገብረመስቀል ከምክትል ርዕሰ መስተዳድርነታቸው በተጨማሪ የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸውን አስታውቋል። በነሐሴ 2015 ዓ.ም የተመሰረተውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ተስፋዬ ይገዙ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)