ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት 10. 5 ቢሊዮን ዶላር ልታገኝ እንደምትችል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገለጹ 

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ከዓለም ባንክ ጋር የምታደርገው ድርድር ከተሳካ፤ 10.5 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። መንግስታቸው ገንዘቡን ካገኘ፤ ዛሬ በጸደቀው የፌደራል መንግስት በጀት ላይ ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ጥቆማ ሰጥተዋል።

የፌደራል መንግስት ለ2017 ያዘጋጀው በጀት 971.2 ቢሊዮን ብር ነው። በጀቱ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። 

በዚሁ ስብሰባ ላይ የተገኙት  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ መንግስታቸው የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስለሚያደርገው ድርድር ማብራሪያ ሰጥተዋል። መንግስታቸው ከIMF እና ከዓለም ባንክ ጋር ላለፉት አምስት ዓመታት “ሰፊ ንግግር፣ ድርድር እና ውይይት” ሲያደርግ መቆየቱንም አብይ አስታውሰዋል።  

ኢትዮጵያ ተግባራዊ በምታደርጋቸው “የሪፎርም አጀንዳዎች” ላይ የተደረገው ድርድር ይህን ያህል ጊዜ የወሰደው “እኛም አስቸጋሪዎች፤ እነሱም አስቸጋሪዎች በመሆናቸው ነው” ብለዋል። “አሁን አንዳንድ ወዳጅ ሀገራት ባደረጉልን ድጋፍ፤ አብዛኛው ሃሳቦቻችን ተቀባይነት እያገኙ ይመስላል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ ሊያገኝበት የሚችለው ድርድር እየተገባደደ ነው የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቆም አድርገዋል።

“ይህ ጉዳይ ተሳክቶ ሪፎርሙን ካጸደቅን፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት ተጨማሪ 10.5 ቢሊዮን ዶላር  ታገኛለች” ሲሉ አብይ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። ተስፋ የተደረገበት ገንዘብ ከተገኘ፤ በፌደራል መንግስት በጀት ላይ “ይህን ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያዎች ሊደረጉ ይችላሉ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)