የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ እና ወታደር ዜጎችን “በጅምላ አይገድልም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ከወታደራዊ “ስነ ምግባር ደንብ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል” የተባሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተከስሰው በእስር ቤት እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 በተካሄደ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥያቄ ያቀረቡት 16 የፓርላማ አባላት ሲሆኑ ሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ናቸው።
የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባሉ አቶ አበባው ደሳለው፤ መንግስት “የህሊና እስረኞችን ለመፍታት፣ የጅምላ ግድያ እና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን ወስኗል?” ሲሉ ጠይቀዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ በማድረግ የመንግስት ኃይሎች ባለፉት 10 ወራት “ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል” ሲሉ ያሉት አቶ አበባው፤ ከጥሰቶቹ ውስጥ “የጅምላ ግድያ” እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች “ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ወንጅለዋል። ለዚህ በማሳያነትም በእርሳቸው ምርጫ ክልል ጅጋ፣ በፍኖተሰላም፣ በመርዓዊ፣ በደብረ ኤልያስ፣ በደብረሲና፣ ጎንደር እና ወሎ ተፈጽመዋል ያሏቸውን ግድያዎች ጠቅሰዋል። ጾታዊ ጥቃት እና ድብደባን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውንም አቶ አበባው አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ በሰጡት ምላሽ “የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ወታደር በጅምላ አይገድልም” ሲሉ ተከላክለዋል። “እንዴት አድርገን ህዝባችንን እንገድላለን?። ማነው እራሱን የሚገድለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማለት እኮ ሁሉም ነው” ሲሉም ጥያቄ አዘል ምላሽ ሰጥተዋል።
ጉዳዩ የሚነሳው በውጊያ ላይ ካሉ ኃይሎች ጋር በተያያዘ መሆኑን ሲያመለክቱም፤ “በጅምላ ሞትኩ’ የሚለው፤ በጅምላ ለማሸነፍ ይነሳና ሲሞት ነው” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ሆኑ የመንግስት ኃይሎች በዜጎች ላይ ግድያ አይፈጽሙም ቢሉም፤ በዚሁ ንግግራቸው “ስህተት ሊፈጽም” እንደሚችል ግን አምነዋል። “ማንኛውም ስህተት ከተፈጸመ ኃላፊነት ወስደን እናርማለን” ሲሉ አብይ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
“ለተፈጠሩ ስህተቶች፣ በየቦታው ለሚያጋጥሙ ስህተቶች፣ በጣም በጣም የተሻለ ethical ሰራዊት ያለን ቢሆንም ግለሰብም ቢሆን ችግር ከፈጠረ መጠየቅ አለበት” ሲሉም ተደምጠዋል። ከወታደራዊ ስነ ምግባር ደንብ ውጪ “በማይገባ መንገድ ኦፕሬሽን ሰርታችሁል” የተባሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተከስሰው በእስር ቤት እንደሚገኙ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
“የጅምላ ግድያን” አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡት የፓርላማ አባል፤ “የጅምላ እስርን” በተመለከተም ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል። ይህን መሰሉ እስር በአማራ ክልል፤ በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ እንደሚፈጸም አመልክተዋል። የፓርላማ አባሉ “ለወራት በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ” ሲሉ በጥያቄያቸው ካነሷቸው ውስጥ የምክር ቤት አባላት፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና አንቂዎች ይገኙበታል።
“የምክር ቤት አባላትን ስናነሳ፤ የምክር ቤት አባላችን አቶ ክርስቲያን ታደለ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኖ መንግስትን ከምዝበራ ያዳነ፣ በሰላማዊ ትግልም በእጅጉ የሚያምን ሰው ነው። አንድ አመት ለሚሞላ ጊዜ በእስር እየማቀቀ ነው ያለው” ሲሉ አቶ አበባው የፓርቲያቸውን የፓርላማ ተመራጭ አስታውሰዋል።
“ሌሎችም በለውጡ ከእርሶ ጋር አብረው የሰሩ፤ እንደ አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና አቶ ታዬ ደንደአ ያሉም ‘ለውጡ ስህተት ፈጽሟል፤ በትክክለኛው ጎዳና እየሄደ አይደለም’ ብለው ስለሞገቱ ብቻ ለወራት ታስረዋል” ሲሉም የአብን የፓርላማ አባሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ተናግረዋል።
አቶ አበባው የአማራ ክልል ምክር ቤት እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑትን የአቶ ሀብታሙ በላይነህ ጉዳይንም በማንሳት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማጽኖ አቅርበዋል። የአብን አባሉ አቶ ሀብታሙ “ላለፉት አራት ወራት የት እንደገባ አይታወቅም” ያሉት አቶ አበባው፤ ይህን ጉዳይ ቤተሰቡም እኔም ለተለያየ የመንግስት ኃላፊዎች አቤት ብለናል ምላሽ አላገኘንም። ዛሬ እርሶ ምላሽ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
የአቶ ክርስቲያን እስርን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ “እኔ ዳኛ አይደለሁም። ወንጀለኛ ናቸው። ጥፋተኛ ናቸው ልል አልችልም። የፍትህ ስርዓቱ አይቶ መርምሮ ፈትሾ ፍርድ ይስጥ” ብለዋል። በአቶ ክርስቲያን ላይ “የግል ጥላቻ የለኝም። የግል መገፋትም የለብኝም” ያሉት አብይ፤ “ህግ ከፈታቸውና ከእኛ መካከል ቢሆኑ ደስታውን አልችለውም” ሲሉ ተደምጠዋል።
“በሰላማዊ መንገድ አራት ኪሎ ተቀምጠው ‘ጉዞ ወደ 4 ኪሎ’ ከሚሉ፤ አራት ኪሎ ተቀምጠው ‘ጉዞ ወደ ፓርላማ’ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም”
– አቶ ክርስቲያን ታደለን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተናገሩት የተወሰደ
“በሰላማዊ መንገድ አራት ኪሎ ተቀምጠው ‘ጉዞ ወደ 4 ኪሎ’ ከሚሉ፤ አራት ኪሎ ተቀምጠው ‘ጉዞ ወደ ፓርላማ’ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም” ሲሉም አክለዋል። ሆኖም የፓርላማ አባል፣ ጋዜጠኛ፣ ሚኒስትር፣ የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መሆን “ከወንጀል እና ከጥፋት አይታደገንም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በእነዚህ ቦታዎች ላይ መቀመጥ “ለማንኛውም ጥፋት ዋስትና አድርገው” የሚያዩ እንዳሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተችተዋል። “ዝም ብሎ መንገደኛ ይነሳና፤ ዩቲዩብ ከፍቶ ‘ጋዜጠኛ ነኝ’ የሚለው፤ እንደዚያ ትክክል አይደለም። ጋዜጠኛም ህግ አለው። ሚኒስትርም ህግ አለው። ወታደርም ቢሆን ህግ አለው። መጠየቅ አለበት” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)