የሰብአዊ መብት ተቋማትን እና አሰራራቸውን “መፈተሽ” እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የሰብአዊ መብት አዋጅ፣ ተቋም እና አሰራር መፈተሽ ያስፈልጋል” አሉ።  የሰብአዊ መብት ተቋማት ከሌሎች ሀገራት እና ፍላጎቶች ተጽዕኖ “ነጻ መሆን” እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። 

አብይ ዛሬ ሐሙስ በፓርላማ በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ስብሰባ ላይ “ሰብአዊ መብት ከዋናው የትርጉም ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው” ብለዋል። “ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሚታመሱት በዚህ ታርጋ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰብአዊ መብት ተቋማት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች “ሀገር ሊያፈርስ” እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። 

“እኛ ደመወዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን፤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው” ሲሉም አብይ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። የሰብአዊ መብት ተቋማት ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከውጪ ኃይሎች ተጽእኖ “ነጻ መውጣት” እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። 

“እነዚህ ተቋማት ከሁለት [ወገን] ተጽእኖ ነጻ መውጣት አለባቸው። ከኢትዮጵያ መንግስት ተጽእኖ ነጻ መሆን አለባቸው። እኛ እየገባን እንደፈለግን የምናደርጋቸው መሆን የለባቸውም። ከሌላም ሀገራት እና ፍላጎቶች ነጻ መሆን አለባቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተቋማት ግን “ነጻ የሆኑት” ከመንግስት ተጽእኖ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።

“እኔ በየትም ቦታ ያሉ የሰብአዊ መብት የሚባሉ ሀሳቦች እና ተቋማት የማያቸው፤ ልክ እንደ መርፌ ነው። መርፌ የራሱን ቀዳዳ መስፋት አይችልም። የራሳቸውን ድክመት ማየት አይችሉም። ይሄ ጥሩ አይደለም። ሀገር ያፈርሳል። ጥቅም የለውም። ተቋሞቻችንን ጸዳ ማድረግ አለብን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)