በኢትዮጵያ ምንጩ ያልታወቀ በርካታ ቢሊዮን ብር ሲንቀሳቀስ መገኘቱ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ምንጩ ያልታወቀ፤ “አየር ላይ የሚንቀሳቀስ” “በርከት ያለ ቢሊዮን ብር” ሲንቀሳቀስ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ ዶ/ር አብርሃም በርታ በበኩላቸው “የመንግስት መዋቅር በሌቦች ተጠልፏል” ብለዋል። 

ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 በፓርላማ በተካሄደ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጥያቄ ካቀረቡ የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑትዶ/ር አብርሃም፤ ሙስና በኢትዮጵያ “እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል” ብለዋል።  ስላሉት የሙስና ጉዳይ አንስተዋል። ሙስና በሀገሪቱ “ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን” ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ጭምር ይፋ መደረጉን አመልክተዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረበው ዓመታዊ ሪፖርትም፤ “ከፍተኛ የሆነ የሃገር ሀብት ብክነት እንዳለ” በዝርዝር በማስረጃ አስደግፎ ማቅረቡንም ጠቅሰዋል። “በኦዲተር ሪፓርት መሰረት በየመስሪያ ቤቶቹ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ይታያል። ገንዘብ ያለማስረጃ ወጪ በማድረግ ይጠቀማሉ። ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርብ በወጪ ይመዘግባሉ። ከፋይናንስ መመሪያና ደንብ ውጪ የገንዘብ ክፍያ ይፈጸማል” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል።

መንግስት ሙስናን ለመዋጋት “ይህ ነው የሚባል መፍትሄ እየሰጠ አይደለም” ሲሉም ተችተዋል። “የህዝብና የመንግስት ሃብት በዘረፉ ሙሰኛ ባለስልጣናት ላይ መቀጣጫ የሚሆን እርምጃን ከመውሰድ ይልቅ ተጨማሪ ሹመትና የቦታ ዝውውር በመስጠት መንግስት ሙሰኞችን አብሮ አቅፎ ይኖራል ማለት ይቻላል። ከዚም የተነሳ የመንግስት መዋቅር በሌቦች ተጠልፏል” ሲሉ ዶ/ር አብርሃም ወንጅለዋል።

በኢትዮጵያ “የሌብነትን ችግር” ለመቅረፍ “አፋጣኝና አስተማሪ የሚሆን እርምጃ” መወሰድ እንዳለበት የፓርላማ አባሉ አሳስበዋል። አሁን በስራ ላይ ያለውን “የጸረ ሙስና ህግ” ተሻሽሎም ቢሆን ችግሩ ካልተቀረፈ፤ “በሃገራችን አሁን የምናያቸው ፈተናዎች ተደምረው፤ ሙስና የሃገራችንን ህልውና መፈተኑ የማይቀር ጉዳይ ነው” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የሙስናን ችግር ለመፍታት፤ መንግስት “ቃል ከመግባት ያለፈ ምን ተግባዊ እርምጃ ለመውሰድ” እንዳሰበም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ሙስና “ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምልከታ” እንዳለው አስረድተዋል። መንግስታቸው ሙስናን “በተግባር” ለመታገል በቅርቡ ህግ ባዘጋጀበት ወቅት የገጠመውን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ምንጩ ያልታወቀ፤ “አየር ላይ የሚንቀሳቀስ” “በርከት ያለ ቢሊዮን ብር” ሲንቀሳቀስ መገኘቱን በማንሳትም ችግሩን በምሳሌ ለማስረዳት ሞክረዋል።   

“የእነዚህ ብር ምንጫቸው የት ነው? ብለን ስንከተል፤ የገንዘብ ባለቤት ሆነው ያገኘናቸው ሰዎች አርሶ አደሮች እና እንኳን ቢሊዮን፣ ሚሊዮን ብር ያላዩ ሰዎች ናቸው። ምንም በማያውቁ አክስቶች፣ ምንም በማያውቁ አያቶች የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ ገንዘቦች አሉ። ይሄንን ገንዘብ ከየት አመጣኸው? ብሎ የኢትዮጵያ መንግስት መጠየቅ አይችልም። ህግ የለውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። 

“ከፍተኛ ሃብት የሚያንቀሳቅስ ሰው ከየት እንዳመጣው ማስረጃ ማቅረብ አለበት” ያሉት አብይ፤ ይህን በተመለከተ ህግ ሲወጣ ትችቶች መከተላቸውን አንስተዋል። “እንፈትሽ ስንል አየር ላይ  የነበረውን ጫጫታ አይታችኋል። ቁርጠኛ ከሆናችሁ፤ የሚወጡ ህጎች ጤነኞችን ለመንካት አይደለም ሌቦችን ለማረም ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። 

“እርምጃን በሚመለከት በሺህ የሚቆጠር ሰው ታስሯል። በርካታ ሃብት [ለጸረ ሙስና] ኮሚቴ ተመልሷል። ግን በቂ አይደለም። ከዚህ በላይ ስራ ያስፈልጋል። እነዚህ ሰዎች ብር ስላላቸው ዩቱበሩን፣ ፌስቡኩን ይከፍሉና አየሩን ያንጫጩታል። ገና ህጉ ሳይወጣ የተያያዘ ስለሆነ ይንጫጫል። እኛ ደግሞ ሳናጣራ እሱን እናራግባለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“አንዳንድ በትክክል ያልተናበብንባቸው አዋጆች ጥፋት ሊያመጡ ይችላሉ” ሲሉ ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ይህም ሆኑ ግን ሙስና በመዋጋት ረገድ “በመንግስት በኩል ያለ ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም” በማለት ለኢዜማው የፓርላማ አባል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)