ለዘጠኝ ዓመታት በስራ ላይ የቆዩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት፤ በሳምንቱ መጨረሻ ሊሰናበቱ ነው 

በሙሉጌታ በላይ

ከዘጠኝ ዓመት በፊት በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተመርጠው እስካሁን በስራ ላይ የቆዩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት፤ በመጪው እሁድ እንደሚሰናበቱ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የአዲሱ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ የሚካሄድበት ቀን “ባልተሟሉ ጉዳዩች” ምክንያት ገና አለመወሰኑን ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ያሉት አጠቃላይ መቀመጫዎች ብዛት 99 ነው። ሆኖም በሰኔ 2013 ዓ.ም በተደረገው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ “በጸጥታ ችግር ምክንያት” ድምጽ የተሰጠባቸው በ28 መቀመጫዎች ላይ ብቻ ነበር። እነዚህን መቀመጫዎች ሙሉ ለሙሉ ያሸነፈው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው።

በቀሪዎቹ የምክር ቤት መቀመጫዎች ላይ ምርጫ ለማካሄድ በክልሉ የነበረውን የጸጥታ ችግር ባለመቀረፉ፤ ሂደቱ የተከናወነው ከሶስት ዓመት መዘግየት በኋላ ነው። በዚህ መሰረት በክልሉ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ በተካሄደ “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ”፤ ለ71 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ድምጽ ተሰጥቷል።

ከእነዚህ መቀመጫዎች ውስጥ በ60ዎቹ ተወካዮቹን ያስመረጠው ብልጽግና ፓርቲ ነው። የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ስምንት መቀመጫዎች በዚህ ምርጫ ያገኘ ሲሆን ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) በበኩሉ ሶስት መቀመጫዎችን ማሸነፍ ችሏል። 

በሰኔው “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ” የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች አዲስ በተመረጡ ተወካዮች በመሞላቱ፤ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በምክር ቤት አባልነት የቆዩ ተመራጮች እንደሚሰናበቱ ተገልጿል። አዲሱ ምክር ቤት የመጀመሪያ ጉባኤውን ከማካሄዱ እና የክልሉን አዲስ መንግስት ከመመስረቱ በፊት ግን ነባሩ ምክር ቤት ከቅዳሜ ሐምሌ 20፤ 2016 ጀምሮ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄዳል ተብሏል። 

የነባሩ ምክር ቤት አባላት የመጨረሻ ጉባኤያቸውን ከማካሄዳቸው በፊት፤ በነገው ዕለት ለውይይት እንደሚሰበሰቡም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ይህ ስብሰባ በመደበኛ ጉባኤ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ላይ ውይይት የሚደረግበት፣ የክልሉ መንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የሚገመገምበት እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሊመለሱ የሚገቡ ጥያቄዎች ዝርዝር የሚወጣበት እንደሆነ አፈ ጉባኤው አክለዋል።

ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ሐምሌ 20 በሚጀመረው መደበኛ ጉባኤ፤ የክልሉ መንግስት አስፈጻሚ አካላት፣ የክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋና ኦዲተር ሪፖርቶች እንደሚቀርቡ ዶ/ር ተመስገን አስረድተዋል። በመጪው እሁድ በሚኖረው የጉባኤ ውሎ፤ ነባሩ ምክር ቤት የክልሉን የ2017 በጀትን ጨምሮ ሶስት አዋጆችን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። 

በዚሁ ዕለት ነባሩ ምክር ቤት ይፋዊ ስንብት እንደሚያደርግ አፈ ጉባኤው ቢያስታውቁም፤  “የአዲሱ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ የሚደረግበት ቀን አልተወሰነም” ብለዋል። “የአዲሶቹን የምክር ቤት አባላትን የሚገልጽ፤ ከምርጫ ቦርድ የሚላክ መታወቂያ እና ሌሎች  መረጃ ስላልተሟሉ፤ [መረጃው] እንደደረሰ መስራች ጉባኤው ይደረጋል” ሲሉ ዶ/ር ተመስገን አክለዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ የአዲሱ ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባ መከናወን ያለበት የቀድሞው ምክር ቤት የስራ ዘመን በተጠናቀቀ “በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ” መሆኑን ይደነግጋል። የአዲሱን ምክር ቤት የመክፈቻ ስብሰባ የመጥራት ኃላፊነት በደንቡ የተሰጠው፤ ለነባሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሊያም ምክትል አፈ ጉባኤ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)