በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ሰኞ በተከሰተው የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ። እስከ ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 17፤ 2016 ድረስ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 257 ማሻቀቡን ድርጅቱ ገልጿል።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ዛሬ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርት፤ በመሬት ናዳው ከሞቱት በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው 12 ሰዎች በሳውላ ሆስፒታል ህክምና በማግኘት ላይ ይገኛሉ። በአደጋው ቢያንስ 125 ሰዎች መፈናቀላቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ነዋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ማህበረሰብ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁሟል።
አደጋው በደረሰበት ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የሚገኝ አንድ የአይን እማኝ፤ በአካባቢው በተተከሉ ሶስት ድንኳኖች ሰዎች ተጠልለው መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ተጨማሪ ሁለት ድንኳኖችም ዛሬ ረፋዱን መተከላቸውን አስረድተዋል። በድንኳኖቹ ለተጠለሉ ሰዎች ጊዜያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
OCHA በዛሬው ሪፖርቱ፤ ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጡ የሚችሉ 15,515 ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከአካባቢው እንዲለቅቁ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል። የፌደራል መንግስት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከጎፋ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር፤ ነዋሪዎቹን ወደሌሎች ቦታዎች ለማዘዋወር የሚያስችለውን እቅድ በማጠናቀቅ ላይ መሆናችውን ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
የጎፋ ዞን የመሬት ናዳ አደጋ በአለም አቀፍ የዜና አውታሮች ሽፋን ካገኘ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ትኩረት ስቧል። ጉተሬዝ ትላንት ረቡዕ ምሽት በቃል አቃባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ በአደጋው “በጥልቅ ማዘናቸውን” ገልጸዋል። ተመድ እና አጋሮቹ “የሰብአዊ ሁኔታውን ለመገምገም፣ የደረሰውን ጉዳት ለመለየት እና የተጎጂውን ህዝብ የሰብአዊ ፍላጎት ለማወቅ” ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)