የህወሓት ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን፤ የፓርቲው ድርጅታዊ ጉባኤ አካል መሆን እንደማይፈልግ አስታወቀ  

በናሆም አየለ

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ በሐምሌ ወር መጨረሻ ለማካሄድ ባቀደው ድርጅታዊ ጉባኤ አካል መሆን እንደማይፈልግ የፓርቲው ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አስታወቀ።  ድርጅታዊ ጉባኤውን በማካሄድ ለሚመጣ “ማንኛውም አደጋ”፤ የፓርቲው አመራር “ኃላፊነቱን እንደሚወስድም” ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል።

የህወሓትን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ለማዘጋጀት የተቋቋመው ኮሚቴ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማከናወን የሚያስችሉ መርሃ ግብሮችን ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄዱ አስታውቆ ነበር። በመርሃ ግብሩ መሰረት በመጪው እሁድ ሐምሌ 21፤ 2016፤ የህወሓት የታችኛው መዋቅር አባላት በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ምርጫ ያካሄዳሉ። 

እነዚህ ተወካዮች በመጪው ሳምንት ማክሰኞ በወረዳ ደረጃ ከተገናኙ በኋላ በጉባኤው የሚሳተፉ አባላትን እንደሚመርጡም ኮሚቴው ገልጿል። አዘጋጅ ኮሚቴው “ህወሓትን የሚታደግ” ሲል በጠራው በዚህ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን፤ “በንጽህና” እና “በህዝብ ወገንተኝነት” እንደሚርጡም የፓርቲውን አባላት አሳስቧል።

ፎቶ፦ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፌስቡክ የተገኘ

የህወሓት ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን በበኩሉ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 17፤ 2016 ባወጣው መግለጫ፤ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴውን እና የፓርቲውን ማዕከላዊ ኮሚቴ ወቅሷል። ድርጅታዊ ጉባኤውን እንዲያዘጋጅ የተቋቋመው ኮሚቴ፤ በተለያዩ ምክንያቶች “ኢ-ዲሞክራሲያዊ እና “ግልጽነት የጎደለው ነው” ሲል ኮሚሽኑ በመግለጫው ተችቷል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽኑ በጋራ ካስቀመጧቸው ጉዳዮች ውጪ፤ “ዝግጅት እየተደረገ ነው” ሲል ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው ላይ አሰፍሯል። ይህ እንዲስተካከል ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም ለአዘጋጅ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቦ እንደነበር በመግለጫው ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤ ሆኖም ላቀረባቸው ጥያቄዎች “ሰሚ አካል” ማጣቱን አትቷል።

ድርጅታዊ ጉባኤው “‘የበላይነት አለኝ’  በሚል አካል ተጠልፎ አደገኛ አካሄድ ላይ መሆኑን” የገለጸው የቁጥጥር ኮሚሽኑ፤ “የእዚህ አደገኛ አካሄድ አካል ላለመሆን” ውሳኔዎችን ማሳለፉን በመግለጫው ጠቅሷል። በዚህ መሰረት በጉባኤ ዝግጅት ኮሚቴው ተካትተው የነበሩ የቁጥጥር ኮሚሽኑ አባላት ከዚህ በኋላ በሂደቱ እንደማይሳተፉ አስታውቋል። 

የቁጥጥር ኮሚሽኑ “ጤናማ ያልሆነ እና ግልጽነት የጎደለው” ሲል የገለጸውን የጉባኤ ዝግጅት ሂደትም እንዲስተካከል በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጉባኤውን በማዘጋጀት ለሚመጣው ማንኛውም አደጋ ግን “አመራሩ ኃላፊነት ይወስዳል” ሲል የቁጥጥር ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል። 

የህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን “ይመጣል” ያለውን አደጋ በመግለጫው በዝርዝር ባያስረዳም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለ ህወሓት ጉባኤ ከትላንት በስቲያ ከሰነዘሩት ማስጠንቀቂያ ጋር የተዛመደ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያውን ያሰሙት፤ ባለፈው ማክሰኞ ከተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ነበር። 

በዚሁ ውይይት የተሳተፉት የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ አመራር አቶ ከበደ አሰፋ፤ “ህወሓት ከልክ በላይ ወደ ዝርፊያ ገብቶ እንዲፈረጥም፤ በወርቅ፣ በማዕድን፣ በተለያዩ የብረታ ብረት ዘረፋ ተሰማርቶ ራሱን እያጎለበተ መልሶ በማን አለብኝነት ‘ጉባኤ እንዳናደርግ የሚከለክለን ምድራዊ ኃይል የለም’ የሚል በሚዲያ የሚገለጽ መግለጫ እያወጣ [ነው]” ሲሉ ወንጅለዋል። ህወሓት “እንደ ትላንትናው ወደ ፉከራው፣ ወደ በሽታው እየገባ ባለበት ሁኔታ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መከለስ የለበትም ወይ?” ሲሉም ጠይቀዋል።    

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ህወሓት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ህጋዊ ፓርቲ እንዲሆን በፌደራል መንግስት በኩል መከናወን የሚገባቸው ስራዎች “መቶ በመቶ” መፈጸማቸውን አስረድተዋል። “ፓርቲ ለፓርቲ፤ መንግስት ለመንግስት ውይይቶች ነበሩን። ጥያቄዎች ተነስተው መልሰናል” ሲሉም አክለዋል።

“ህወሓት አሁን ማድረግ ያለበት ምርጫ ቦርድ ጋር ሄዶ በሁለት ሶስት ሳምንት ውስጥ የሚጠበቅበትን ዶክመንት አሟልቶ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ጉባኤ ማካሄድ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣዩ ሂደት ምን መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል። ፓርቲው “[ይህንን] ባያደርግ እኔ ብፈልግም ባልፈልግም፤ ዋጋ የለውም። ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው፣ ህጋዊ ፓርቲ ካላለው በምርጫ ሊሳተፍ አይችልም። መንግስት ሊሆን አይችልም” ሲሉም አብራርተዋል።

ህወሓት ህጋዊ መንገዱን ተከትሎ ጉባኤ ካላካሄደ፤ “ተመልሰን ጦርነት እንገባለን ማለት ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ምላሻቸው ላይ አስጠንቅቀዋል። “ተመልሰን ጦርነት ውስጥ ከምንገባ፣ ተመልሰን ጭቅጭቅ ውስጥ ከምንገባ፤ [የሚቀረው] ቀላል ነው። ዋና ዋናው አልቋል። ሕግ ተበጅቷል፣ ተስማምተናል” ሲሉም አብይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ተናግረዋል። 

ፎቶ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስቡክ የተገኘ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የጠቀሱት ህግ፤ “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያደርግ ነው። በ2011 ዓ.ም የጸደቀውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ያሻሻለው ይህ ህግ በፓርላማ የጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ነበር። 

የፍትሕ ሚኒስቴር ይህንኑ አዋጅ መሰረት በማድረግ፤ ህወሓት “በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “አስፈላጊውን ትብብር” እንዲያደርግ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡም ይታወሳል። በዚህ መልኩ ማረጋገጫ ያገኙ የፓለቲካ ቡድኖች፤ ማመልከቻቸውን እና አባሪ ሰነዶችን ለምርጫ ቦርድ ባቀረቡ በ15 የስራ ቀናት ውስጥ ምዝገባው እንደሚፈጸምላቸው በአዋጅ ማሻሻያው ተደነግጓል።  

“ተመልሰን ጦርነት ውስጥ ከምንገባ፣ ተመልሰን ጭቅጭቅ ውስጥ ከምንገባ፤ [የሚቀረው] ቀላል ነው። ዋና ዋናው አልቋል። ሕግ ተበጅቷል፣ ተስማምተናል”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተናገሩት

ለብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ከሚቀርቡት ሰነዶች ውስጥ፤ የፖለቲካ ፓርቲው “ፕሮግራም” እና “የመተዳደሪያ ደንብ” ይገኝበታል። የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች “በኃላፊነት ለመስራት መስማማታቸውን” የሚያስረዳ ሰነድም “በፊርማቸው ተረጋግጦ” መቅረብ እንዳለበት በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተቀምጧል። የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና አድራሻም በምዝገባ ሰነዱ ላይ መካተት እንደሚገባው በአዋጁ ላይ በተጨማሪነት ሰፍሯል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንት በስቲያ ንግግራቸው፤ የቀረውን ጉዳይ አሟልቶ፣ በህጋዊ መንገድ ጉባኤ አካሂዶ፣ ህወሓትን ወደ ፖለቲካ ስርዓት መመለስ ከሁሉ በላይ የሚጠቅመው ለፓርቲው መሆኑን ገልጸው ነበር። ህጋዊ አካሄዱን መከተል ከህወሓት በማስከተል “የትግራይ ህዝብን”፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ “ሁላችንንም ይጠቅማል” ሲሉም ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)