የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነገ ቅዳሜ ሐምሌ 20፤ 2016 ጀምሮ ያሉት ተከታታይ ሶስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆኑ አወጀ። ምክር ቤቱ የሀዘን ቀኑን ያወጀው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ሰኞ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማሰብ ነው።
በጎፋ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት ናዳ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች 257 መድረሳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትላንትናው ዕለት ባወጣው ሪፖርት አስታውቆ ነበር። የሟቾቹ ቁጥሩ እስከ 500 ድረስ ሊያሻቅብ እንደሚችልም ድርጅቱ የአካባቢውን ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
እንዲህ አይነት አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ብሔራዊ ሀዘን የማወጅ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። አደጋው የተከሰተው ፓርላማው በስራ ላይ በማይሆንበት ወቅት ከሆነ፤ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚችሉም በአዋጅ ተደንግጓል።
በዚህም መሰረት የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ በጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ለማሰብ ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ብሔራዊ የሀዝን ቀን ሆኖ እንዲታወጅ መወሰናቸውን ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በእነዚህ የሀዘን ቀናት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ የሚውለበለብ ይሆናል።
የዚህ ውሳኔ ተፈጻሚነት በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በኢትዮጵያ መርከቦች ላይ እንደሚሆን በተወካዮች ምክር ቤት መግለጫ ላይ ተመልክቷል። ውሳኔውን ያሳለፉት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ አደጋውን የደረሰበትን ስፍራ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ሐምሌ 17፤ 2016 በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል።
ከአፈ ጉባኤው ጋር አብረው ወደ ስፍራው የተጓዙት በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዲሁም የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አጽናንተዋል። አደጋው የደረሰበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዛሬው ዕለት በስፍራው በመገኘት በተመሳሳይ ሁኔታ ሀዘናቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)