በቤርሳቤህ ገብረ
በኢትዮጵያ ወርቅ ከሚመረትባቸው አምስት ክልሎች አንዱ የሆነው የጋምቤላ ክልል፤ ለልዩ አነስተኛና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች እና አቅራቢዎች ይሰጥ የነበረውን ፈቃድ “ላልተወሰነ ጊዜ” አቆመ። ከዚህ ቀደም ፈቃድ ከተሰጣቸው አምራቾች እና አቅራቢዎች መካከል የ343ቱን ፈቃድ መሰረዙንም ክልሉ አስታውቋል።
የጋምቤላ ክልል ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በክልሉ ተንሰራፍቷል ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር መሆኑን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙቴ ሎንግ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከክልሉ ወርቅ በኮንትሮባንድ “ወደ መሃል ሀገር” እንደሚሄድ የገለጹት አቶ ሙቴ፤ ታማኝ ለሆኑ እና የወርቅ ምርቱን ወደ ብሔራዊ ባንክ ለሚያስገቡ ግለሰቦች ፈቃድ ለመስጠት በማሰብ ለጊዜው ሂደቱ እንዲቆም መደረጉን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ እንደ ወርቅ እና ብር ያሉትን የከበሩ ማዕድናት የመግዛት እና የመሸጥ ስልጣን በተቋቋመበት አዋጅ ተሰጥቶታትል። ባንኩ የወርቅ እና የብር ግብይትን አስመልክቶ መመሪያዎችን እንደሚያወጣ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተደነገገው መሰረት፤ የወርቅ ግብይት ዋጋን የሚወስን መመሪያ በየጊዜው ሲያወጣ ቆይቷል።
ብሔራዊው ባንክ “ከባህላዊ የወርቅ ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ” በማሰብ፤ ከሚያዝያ 2015 ጀምሮ በስራ ላይ የቆየውን መመሪያ ከአንድ ወር በፊት ማሻሻሉ ይታወሳል። በዚሁ የመመሪያ ማሻሻያ ላይ ባንኩ፤ “በባህላዊ የወርቅ ምርት ዘርፍ በሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች ምክንያት አገሪት ማግኘት የነበረባት የውጭ ምንዛሬ እና ከዘርፉ የሚጠበቁ በርካታ ገቢዎች ከሚጠበቀው በታች እየወረዱ መምጣታቸውን” አስታውቆ ነበር።
የጋምቤላ ክልል የ2016 በጀት ዓመት የወርቅ ግብይት መጠን፤ በብሔራዊ ባንክ የተጠቀሰውን “ከሚጠበቀው በታች” አፈጻጸምን በሚገባ የሚያሳይ ነው። ክልሉ በበጀት ዓመቱ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት በእቅድ ይዞ የነበረው 1,250 ኪሎ ግራም ወርቅ ቢሆንም፤ ለባንክ ማቅረብ የቻለው 310 ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑን አቶ ሙቴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ለብሔራዊ ባንክ የገባውን ይህን የወርቅ መጠን ያቀረቡት፤ 100 የሚጠጉ አምራቾች እና አቅራቢዎች ብቻ መሆናቸውን ምክትል ኃላፊው አመልክተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ በባህላዊ ወርቅ አምራችነት ፍቃድ ያገኙ ሲሆን 80 ገደማ የሚሆኑት በልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራችነት የተመዘገቡ መሆናቸውን ከክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጋምቤላ ክልል በኩባንያ ደረጃ ወርቅ የሚያመርት አንድ ድርጅት ብቻ ሲሆን ወርቅን ለማምረት እና ለማቅረብ ፈቃዱ ያገኙ ግለሰቦች እና ማህበሮች ከ500 ይልቃሉ። በክልሉ ለልዩ አነስተኛ እና ባህላዊ ወርቅ አምራችነት የሚሰጠው ፈቃድ ለሁለት እና አምስት አመት የሚያገለግል ነው።
የጋምቤላ ክልል በተገባደደው 2016 በጀት አመት “ደካማ አፈጻጸም አሳይተዋል” ያላቸውን 343 ልዩ አነስተኛና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች እና አቅራቢዎች ፈቃድ መሰረዙን አቶ ሙቴ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ከ1.5 ኪሎ ግራም በታች ላቀረቡ ወርቅ አምራቾች እና አቅራቢዎች “የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ” እንዲደርሳቸው መደረጉንም የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ምክትል ኃላፊ አክለዋል።
የልዩ አነስተኛ እና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች የአሰራር ሁኔታን ለመቆጣጠር ያለመ “የማዕድን ስራ ደንብ”፤ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ሙቴ ጠቁመዋል። ይህ ደንብ በልዩ አነስተኛና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች እና አቅራቢዎች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶችን ያካተተ መሆኑንም አመልክተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለብሔራዊ ባንክ ከገባው 3.023 ቶን ውስጥ፤ ባህላዊ አምራቾች ያቀረቡት 0.6 ቶን ብቻ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ባለፈው ግንቦት ወር አስታውቆ ነበር። ይህ የወርቅ ምርት መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የ12.6 በመቶ ብልጫ ያሳየ” መሆኑም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሆኖም የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ከሁለት አመት በፊት ከነበረው እና በማዕድን ሚኒስቴር ከታቀደው ጋር ሲነጻጸር “በከፍተኛ መጠን መቀነሱ” በፓርላማ ስብሰባዎች ጭምር ሲያነጋግር ቆይቷል። የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ ባለፈው ግንቦት ወር ለፓርላማ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ የሀገሪቱ የወርቅ ምርት በእቅድ ከተያዘው አንጻር ዝቅ ካለባቸው ምክንያቶች መካከል የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የህገወጥ ግብይት፤ የጸጥታ ችግር ዋነኞቹ መሆኑን ጠቅሰው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)