ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ በአዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ሹመት አገኙ

በሙሉጌታ በላይ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሁለት ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ አዲስ በተመሰረተው የክልሉ ካቢኔ ተካትተው ሹመት አገኙ። ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) በበኩሉ በካቢኔው “እንደምንካተት የተገባልን ቃል አልተፈጸመም” ሲል ቅሬታ አቅርቧል።

ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 23፤ 2016 መስራች ጉባኤውን ያደረገው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት፤ ላለፉት 8 ዓመታት ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩትን አቶ አሻድሊ ሀሰንን በድጋሚ በርዕሰ መስተዳድርነት ሾሟል። የክልሉ ምክር ቤት በአቶ አሻድሊ የቀረቡ 19 የካቢኔ አባላትን ሹመትም አጽድቋል።

ሹመት ካገኙት የካቢኔው አባላት መካከል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉን ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ በኃላፊነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ጌታሁን አብዲሳ ይገኙበታል። አቶ ጌታሁን በኃላፊነት ከሚመሩት ቢሮ በተጨማሪ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሆነው እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

በአዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ካቢኔ ውስጥ የቦሮ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ቦዴፓ) እና የቤንሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) አመራሮችም ተካትተዋል። ቦዴፓ ባለፈው ሰኔ ወር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተካሄደው “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ”፤ ስድስት ክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን እና አንድ የፓርላማ ወንበር ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ከተመረጡት የቦዴፓ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ፓርቲው ከተመሰረበት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሊቀመንበርነት እየመሩ ያሉት አቶ አመንቴ ገሺ ይገኙበታል። አቶ አመንቴ በትላንቱ ጉባኤ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮን ኃላፊነት እንዲመሩ ተሹመዋል። 

አቶ አመንቴ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ ከጅማ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በተማሩበት የህግ ዘርፍ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዐቃቤ ህግነት እና በጥብቅና ያገለገሉት አቶ አመንቴ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በ“ሊደርሺፕ” ከሊድ ስታር ኮሌጅ ተቀብለዋል። 

የቦዴፓው ሊቀመንበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ በ2014 ዓ.ም ተሹመው ነበር። አቶ አመንቴ ይህን ተቋም ለአንድ ዓመት ያህል ከመሩ በኋላ፤ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በተመሳሳይ የኃላፊነት ደረጃ ወደ ክልሉ የገጠር መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ተዘዋውረው እስከ አዲሱ ሹመታቸው ድረስ ሲሰሩ ቆይተዋል።  

እንደ ቦዴፓ ሁሉ ቤህነንም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው ከአዲሱ ሹመት ቀደም ብሎ ነበር። የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አብዱሰላም ሸንግል የክልሉን የስራ እና ክህሎት ቢሮን እንዲመሩ የተሾሙት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ነበር። 

የቤህነን ሊቀመንበር ሹመቱን ያገኙት ፓርቲው ከክልሉ መንግስት ጋር “በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን” ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ ነው። በትላንትናው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ላይ፤ አቶ አብዱሰላም ለአንድ አመት በቆዩበት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የቀረበው የሹመት ጥያቄ ጸድቋል። 

አቶ አብዱሰላም ከተመሰረተ ከ40 ዓመታት በላይ የሆነው ቤህነንን የተቀላቀሉት በ2007 ዓ.ም. ነበር። ለአምስት ዓመታት በአባልነት ከቆዩ በኋላ በ2012 ዓ.ም. የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆን እስካሁንም በዚሁ የአመራርነት ድርሻ እየሰሩ ይገኛሉ። ሊቀመንበሩ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢም ናቸው።  

እንደ ቤህነን እና ቦዴፓ ሁሉ፤ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄም (ጉህዴን) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት እንደሚካተት “ቃል ተገብቶለት” እንደነበር የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ጉህዴን ባለፈው ሰኔ ወር በክልሉ በተካሄደው “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ”፤ ስምንት የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫዎች እና አንድ የፓርላማ ወንበር ያሸነፈ ነው። 

ጉህዴን  በጫካ ሲያደርግ የቆየውን የትግል በማቆም፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረመው በ2015 ዓ.ም ነበር። ይህንኑ ተከትሎ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ግራኝ፤ የክልሉ የህዳሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።

ሁለት አመት ለሚጠጋ ጊዜ በዚሁ ኃላፊነት የቆዩት አቶ ግራኝ፤ በትላንትናው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ የፍትህ፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል። የክልሉ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ግራኝ ይህ ሹመት ቢሰጣቸውም፤ በአዲሱ የክልሉ ካቢኔ ምስረታ ፓርቲያቸው “ሳይካተት መቅረቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው” አልሸሸጉም። 

ጉህዴን ከክልሉ መንግስት ጋር ከአንድ ሳምንት በፊት ባደረገው ውይይት፤ “ሁለት የካቢኔ ወንበር እንሰጣችኋለን የሚል ቃል ተገብቶልን ነበር” ሲሉም ሊቀመንበሩ ለቅሬታቸውን መነሻ የሆነውን ምክንያት አስረድተዋል። የጉሙዝ ህዝብን የሚወክለው ፓርቲው፤ የካቢኔ ድርሻው ከዚህም በላይ ከፍ ማለት እንዳለበት በስብሰባው ላይ አንስቶ እንደነበር አቶ ግራኝ አስታውሰዋል። 

“ከህዝባችን ብዛት አንጻር ሲታይ የተመጣጠነ አይደለም ብለን ሶስት አድርጋችሁ ስጡን አልን። ‘እናንተም ተመካከሩ እኛም እንመካከራለን’ ብለው ከሸኙን በኋላ፤ ትላንትና መልስ ሳይሰጡን፤ ጉባኤ እንደገቡ በራሳቸው ካቢኔ አደራጅተው መጨረሳቸውን [አየን]” ሲሉ የጉህዴን ሊቀመንበር ሂደቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። 

“ቃላቸውን ያጠፉበትን ምክንያት አላወቅንም” የሚሉት አቶ ግራኝ፤ ፓርቲያቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ቅሬታ የሚገልጽ ደብዳቤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለማስገባት እንዳቀደ ተናግረዋል። የጉህዴን ቅሬታ በተመለከተ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳን እና ሌሎች የክልሉን መንግስት ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)