በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ያገኘውን ድጋፍ እና ብድር የያዘ ተጨማሪ በጀት፤ በቅርቡ ለፓርላማ አቅርቦ እንደሚያስጸድቅ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። ተጨማሪ በጀቱ ለዝቅተኛ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች ለሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ እንዲሁም ለነዳጅ፣ ዘይት፣ ማዳበሪያ እና መድኃኒት ድጎማ የሚውል መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 24፤ 2016 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት የዛሬውን አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው፤ ዓለም አቀፉ የመንግስት ልማት ማህበር ለኢትዮጵያ መንግስት የሰጠውን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የብድር እና ድጋፍ ስምምነት ለማጽደቅ ነበር።
ከዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላሩ ለኢትዮጵያ መንግስት በእርዳታ የተሰጠ ሲሆን ቀሪው 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደግሞ በብድር መልክ የተገኘ ነው። ከአለም አቀፉ የልማት ማህበር የተገኘው ብድር እና እርዳታ “ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ወደ መንግስት ግምጃ ቤት የሚፈስ” እንደሆነ ስምምነቱን ለማብራራት የቀረበው መግለጫ ያስረዳል።
በዚህ መልክ ወደ ግምጃ ቤት “በቀጥታ የገባው” ገንዘብም፤ “የፌደራል በጀትን በተሟላ ሁኔታ ፋይናንስ ለማድረግ” እንደሚውልም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታው ስምምነት በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀ “በሰአታት ውስጥ”፤ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር የባንክ ሂሳብ የሚገባ እንደሆነ አቶ አህመድ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
“[ይህ] 1.5 ቢሊዮን ዶላር የዛሬ አንድ ወር በጀታችንን ስናውጅ ያልነበረ ገቢ ስለሆነ፤ እንደገና ወደ ምክር ቤት መጥተን እናሳውጃለን ማለት ነው። ገንዘብ ሚኒስቴር ይህን ገንዘብ ስራ ላይ የሚያውለው፤ በተጨማሪ በጀት መልክ ይሄው ምክር ቤት ሲያውጀው ብቻ ነው” ሲሉም የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ለፌደራል መንግስት የ2017 በጀት ያጸደቀው የገንዘብ መጠን 971.2 ቢሊዮን ብር ነበር።
አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋው ይህ በጀት ከዚህ ቀደም በፓርላማው ከጸደቁት ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከ ከዓለም አቀፍ አብዳሪ ተቋማት ያገኛቸውን ብድር እና እርዳታ ያካተተ ተጨማሪ በጀት ለፓርላማ በሚያቀርብበት ወቅት፤ በጀቱ አንድ ትሪሊዮንን ሊሻገር እንደሚችል የገንዘብ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ጥቆማ ሰጥተዋል። “የዘንድሮው በጀታችን በጣም በጣም ከፍተኛ ነው የሚሆነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተጨማሪ በጀት ውስጥ ከሚያካትታቸው ገቢዎች ውስጥ፤ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያገኘው ብድር ይገኝበታል። የIMF ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሐምሌ 22፤ 2016 ባካሄደው ስብሰባ፤ ለኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁ ይታወሳል።
የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) በተባለው ፕሮግራም ከጸደቀው ከዚህ ብድር ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህሉ “በአፋጣኝ ለኢትዮጵያ የሚለቀቅ” እንደሆነ ተቋሙ አስታውቆ ነበር። “ከIMF ከተገኘው 3.5 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ በመጀመሪያ ዙር የሚፈስሰው 30 ፐርሰንቱ፤ ለገንዘብ ሚኒስቴር ለበጀት ጥቅም የሚውል ነው። ጥቅም ላይ የሚውለው፤ እዚህ መጥተን ተጨማሪ በጀት ሲታወጅ ነው” ሲሉም የገንዘብ ሚኒስቴሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
ተጨማሪ በጀቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ፤ ለደመወዝ ጭማሪ እና ነዳጅን ጨምሮ ለተለያዩ ሸቀጦች ድጎማ የሚውል መሆኑን አቶ አህመድ አስታውቀዋል። የደመወዝ ጭማሪው የሚደረግላቸው ዝቅተኛ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች፤ ለኑሯቸው መደጎሚያ እንዲሆን ታስቦ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስት ለ2017 ያዘጋጀው በጀት በፓርላማ በጸደቀበት ዕለት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበጀቱ ላይ ማሻሻያዎች ሊደረግ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተው ነበር። ይህ የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ከIMF እና ከዓለም ባንክ ጋር የሚያደርገው ድርድር ከተሳካ እንደሆነም በወቅቱ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
እርሳቸው የሚመሩት መንግስት፤ ከዚህ ቀደምም ተጨማሪ በጀት ለፓርላማ አቅርቦ አጸድቆ ያውቃል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ “በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ” የተባለለትን 561.7 ቢሊዮን ብር የ2014 በጀት ካጸደቀ ከሶስት ወራት በኋላ፤ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማጽደቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]