ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግዢ ክፍያን የሚፈጽመው፤ ራሱ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን መሆኑን አስታወቀ

ወርቅ ለሚያቀርቡ አምራቾች እና አቅራቢዎች ክፍያ የሚፈጸመው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተሰልቶ መሆኑን ባንኩ አስታወቀ። ብሔራዊ ባንክ በወርቅ መግዣ ላይ አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ያደረገው፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ የሚመራ መደረጉን ተከትሎ ነው።

የውጭ ምንዛሬ ተመን “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት” መሸጋገሩ ይፋ የተደረገው ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሐምሌ 22፤ 2016 ነበር።  እንደ ወርቅ እና ብር ያሉትን የከበሩ ማዕድናት የመግዛት እና የመሸጥ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ በዓለም የወርቅ ዋጋ ላይ ማበረታቻዎችን በማከል ወርቅን ከአምራቾች እና ከአቅራቢዎች ሲገዛ ቆይቷል።

ባንኩ ባለፈው ሰኔ ወር ይፋ ባደረገው መመሪያ፤ በዓለም ገበያ ዋጋ ላይ ከ60 እስከ 72 በመቶ ማበረታቻ ጭማሪ በማድረግ የወርቅ ግዢ እንደሚፈጸም ገልጾ ነበር። ብሔራዊው ባንክ ዛሬ ሐምሌ 24፤ 2016 ባወጣው መግለጫ፤ “ለማንኛውም ወርቅ አቅራቢ ክፍያ የሚፈጸመው፤ የእለቱን ዓለም ዓቀፍ የወርቅ ዋጋ በእለቱ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣዉ የውጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ” እንደሆነ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)