በእንግሊዝ፣ ቤልጄየም እና ካናዳ የተሾሙት አዲሶቹ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እነማን ናቸው? 

በተስፋለም ወልደየስ

ኢትዮጵያ በእንግሊዝ፣ ቤልጄየም እና ካናዳ ለሚገኙ ኤምባሲዎቿ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ዲፕሎማቶችን በባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት ሾመች። አዲስ አበባ በሚገኘው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስር ያሉ የስራ ክፍሎችን የሚመሩ ሰባት ዲፕሎማቶችም የአምባሳደርነት ሹመት አግኝተዋል። 

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለ10 ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች እና ለ14 አምባሳደሮች ሹመት መስጠታቸው ይፋ የተደረገው ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ሆኖም ዲፕሎማቶቹ ቃለ መሃላ የፈጸሙት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሐምሌ 25፤ 2016 ነው። 

ኢትዮጵያን በውጭ ሀገራት የሚወክሉ አምባሳደሮች እና ሌሎች መልዕክተኞች በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚሾሙት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት እንደሆነ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ይደነግጋል። አምባሳደሮቹ በፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ከመፈጸማቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው የስራ መመሪያ ተቀብለዋል። 

ባለፈው ግንቦት ሹመት ያገኙት አምባሳደሮች ሐምሌ 25፤ 2016 ቃለ መሃላ ፈጽመዋል | ፎቶ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ከአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ውስጥ አስራ አራቱ በተለያዩ ሀገራት መመደባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቃባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አምባሳደሮቹ ከተሾሙባቸው ሀገራት መካከል እንግሊዝ፣ ቤልጄየም፣ ካናዳ፣ ብራዚል እና ህንድ ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት ካሏት ኤምባሲዎች ውስጥ በደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ አልጄሪያ እና ሞሮኮ ለሚገኙቱ አዲስ አምባሳደሮች መሾማቸው ተገልጿል።

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ብሩክ መኮንን፤ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ጽህፈት ቤት ውስጥ አገልግለዋል። አምባሳደር ብሩክ አዲሱን ሹመት ከማግኘታቸው አስቀድሞ በለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላለፉት አምስት አመታት በተለያዩ ደረጃዎች ሰርተዋል።

ብሩክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላለፉት 22 ዓመታት ማገልገላቸውን ከመስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አዲሱ ተሿሚ ላለፉት ሶስት አመታት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትን ተፈሪ መለስን የሚተኩ ናቸው። ብሩክ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙ ስምንተኛው ዲፕሎማት ናቸው።    

በቤልጄየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ካገለገሉት ውስጥ የኢህአዴግ ጉምቱ ባለስልጣናት የነበሩት ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣ ካሱ ኢላላ እና ተሾመ ቶጋ ይገኙበታል | ፎቶ፦ በቤልጄየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ

እንደ ለንደኑ ኤምባሲ ሁሉ፤ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቁልፍ ከሚባሉ ቦታዎች መካከል በቤልጄየም ብራስልስ የሚገኘው ኤምባሲ ተጠቃሽ ነው። በኤምባሲው በአምባሳደርነት ካገለገሉት ውስጥ የኢህአዴግ ጉምቱ ባለስልጣናት የነበሩት ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣ ካሱ ኢላላ እና ተሾመ ቶጋ ይገኙበታል። በዲፕሎማሲው መስክ ከ35 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ግሩም አባይም በዚሁ ኤምባሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ።  

ከቤልጄየም እና ሉግዘምበርግ ሀገራት በተጨማሪ በብራስልስ በሚገኙ የአውሮፓ ህብረት ተቋማት ኢትዮጵያን የመወከል ኃላፊነት የተጣለበትን የባለ ሙሉ አምባሳደርነት ቦታ ላለፉት አምስት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ይዘው የቆዩት ሂሩት ዘመነ ናቸው። አምባሳደር ሂሩት ወደዚህ ቦታ ከመምጣታቸው በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ። 

እንደ እርሳቸው ሁሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሶስት አስርት አመታትን የተሻገረ አገልግሎት ያላቸው አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ተተኪያቸው እንዲሆኑ በአዲሱ ሹመት ተመድበዋል። አምባሳደር እሸቴ በግብጽ እና በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ጽህፈት ቤት ውስጥ ሰርተዋል። 

አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን እስከ ሹመታቸው ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት መርተዋል | ፎቶ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አምባሳደር እሸቴ የባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት ሹመት ከማግኘታቸው አስቀድሞ በነበሩት አመታት፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። በሚኒስቴሩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄነራል የነበሩት አምባሳደር እሸቴ፤ እስከ ሹመታቸው ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት መርተዋል።

በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ሆነ በመንግስት ስልጣን ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች በአምባሳደርነት የሚሾሙበት ሌላኛው ሀገር ካናዳ ነው። የቀድሞው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ቁልፍ ሰው እና ሚኒስትር የነበሩት አስቴር ማሞ፤ የአሁኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ እና የወቅቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር ናሲሲ ጫሊ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ።  

ስድስት አመት ለሚጠጋ ጊዜ በካናዳ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ፍጹም አረጋም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ የልዩ ጽህፈት ቤታቸው የመጀመሪያው ኃላፊ የነበሩ ናቸው። አቶ ፍጹምን የሚተኳቸው ላለፉት 18 ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዲሁም በታንዛንያ እና በጀርመን በሚገኙ ኤምባሲዎች የሰሩት አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ናቸው።

አምባሳደር ነብዩ ተድላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቃባይ | ፎቶ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በውጭ ሀገራት የተመደቡት አምባሳደሮች፤ የተቀባይ ሀገራት ስምምነትን እንዳገኙ ስራቸውን እንደሚጀምሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቃባይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። እርሳቸውን ጨምሮ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በስራቸው ላይ እያሉ የአምባሳደርነት ሹመት ያገኙ ሰባት ዲፕሎማቶች በያዙት ኃላፊነት እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል። 

ሃያ አራቱም አምባሳደሮች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መሾማቸው፤ ከዚህ ቀደም ይደረጉ ከነበሩት ተመሳሳይ ሹመቶች የተለየ እንደሚያደርገውም ቃለ አቃባዩ አስረድተዋል። አዲሶቹ አምባሳደሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ10 ዓመት እስከ 30 ዓመት የአገልግሎት ዘመን ያላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል። ዲፕሎማቶቹ የአምባሳደርነት ሹመት ያገኙት “ሀገር እና ህዝብን ለማገልገል ባላቸው ታማኝነት፣ በትምህርት ዝግጅታቸው እና የስራ ልምዳቸው፣ የሚሰጣቸውን ስራ በትክክል መተግበር ይችላሉ ወይ?” በሚሉ መለኪያ ተመዝነው እንደሆነም አብራርተዋል።   

ሹመቱ “የመንግስትን አመራር ውሳኔ የሚያመለክት ነው” ያሉት አምባሳደር ነብዩ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት፤ ‘በውጭ ጉዳይ ውስጥ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ይህን ስራ ሊመሩ ይገባል’ የሚል አስተሳሰብ ስለታመነበት ያ እንዲደረግ ሆኗል” ብለዋል። “ይሄ በአምባሳደሮቹ ላይ፣ በዲፕሎማቶቹ ላይ የሚጣለውን ኃላፊነት ከፍተኛ ያደርገዋል። በዚያው ልክ ብዙ ይጠበቅብናል ማለት ነው” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)