በወላይታ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ በተከሰተ የመሬት ናዳ የ12 ሰዎች ህይወት አለፈ

በሙሉጌታ በላይ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ወላይታ ዞን ባሉ ሁለት ወረዳዎች ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 29፤ 2016 በተከሰተ የመሬት ናዳ የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቀ። በዞኑ በካዎ ኮይሻ ወረዳ፣ ጤፓ ቀበሌ በደረሰው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም መምሪያው ገልጿል።

በጤፓ ቀበሌ የመሬት ናዳ አደጋ የደረሰው፤ ከትላንት እሁድ ማታ ጀምሮ በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሆኑን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ባለሙያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በቀበሌው ዛሬ ረፋድ አምስት ሰዓት ገደማ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት “እስካሁን በተደረገ ፍለጋ የ11 ሰዎች አስክሬን መገኘቱን” መምሪያው ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። 

በተመሳሳይ ሁኔታ በወላይታ ዞን፣ ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ፣ ማንአራ ቀበሌ ዛሬ ጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ በደረሰ የመሬት ናዳ፤ የ13 ዓመት አዳጊ ህይወቷ ማለፉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስምኦን ሳፓ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በአደጋው በአንዲት የ18 ዓመት ወጣት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱንም አክለዋል። 

በማንአራ ቀበሌ በደረሰው የመሬት ናዳ 100 የአካባቢው ነዋሪዎች ያለመጠለያ መቅረታቸውን አቶ ስምኦን አስረድተዋል። ነዋሪዎቹ ለጊዜው በቀበሌው ባለ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲጠለሉ መደረጉንም የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ጠቁመዋል።

የኪንዶ ኮይሻ እና ካዎ ኮይሻ ወረዳዎች በሚገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት ናዳ አደጋ ሲያጋጥም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ክልሉ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ ተመሳሳይ የመሬት ናዳ አደጋ ከሁለት ሳምንት በፊት አስተናግዷል። በክልሉ በሚገኘው ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15 በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 231 ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል።  

የሟቾቹን ቁጥር 257 የሚያደርሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በአደጋው ቢያንስ 125 ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል። በአካባቢው ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ ሰዎች ብዛት 15 ሺህ ገደማ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ በወቅቱ ባወጣው መረጃ አመልክቶ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)