በሙሉጌታ በላይ
በጉሙሩክ ኮሚሽን “ተይዘው” የነበሩ የስኳር እና የምግብ ዘይት ምርቶች ከነገ ጀምሮ ተለቅቀው ወደ ገበያ እንደሚወጡ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ “የአቅርቦት እና የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት” መንግስት “በቂ ዝግጅት” ማድረጉንም ገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ አርብ ሐምሌ 26፤ 2016 ባወጣው መረጃ፤ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር መለወጡን ተከትሎ ገበያውን ለማረጋጋት በመንግስት በኩል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሀገሪቱ ሲሰራበት የቆየው የውጭ ምንዛሬ ተመን፤ “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት” መሸጋገሩን ያስታወቀው ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 22፤ 2016 ነበር።
ባንኩ ይህን መግለጫ በሰጠ በሰዓታት ውስጥ በተለይ ከውጭ ሀገር በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ከእነዚህ ሸቀጦች ውስጥ ከ30 እስከ 400 ብር የደረሰ የዋጋ ጭማሪ የታየው በምግብ ዘይት ላይ ነው። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ሆነው ባለፈው ወር የተሾሙት ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፤ “ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ምርትን በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ” መግለጻቸውን መስሪያ ቤታቸው አስታውቋል።
ሚኒስትሩ ነጋዴዎች “እንደዚህ አይነት ድርጊት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ” ማሳሰባቸውንም በመስሪያ ቤታቸው የተሰራጨው መረጃ ጠቁሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 26፤ 2016 በሰጡት ማብራሪያ ላይ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ “ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል፤ እርምጃ ይወሰዳል” ብለው ነበር።
“መዝረፍ እና መቀማት አይፈቀድም” ያሉት አብይ፤ የገበያ ስርዓቱን የሚቆጣጠር “ግብረ ኃይል” መዘጋጀቱን ተናግረዋል። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩም በዛሬው ዕለት ይህንኑ አስተጋብተዋል። ነጋዴዎች ምርቶችን “መደበቅ እና ማከማቸት” ለኪሳራ የሚዳርጋቸው መሆኑን አውቀው፤ ከድርጊቱ እንዲታቀቡ ዶ/ር ካሳሁን አሳስበዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዚህም በተጨማሪ የዘይት አቅርቦት ወደ ገበያ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። ሚኒስቴሩ እንደ ዘይት እና ስኳር የመሳሰሉ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚያስመጡ ነጋዴዎች ጋር በዛሬው ዕለት ባደረገው ውይይት፤ “ከታክስ ክፍያ ጋር” በተያያዘ ያጋጠማቸው ችግር መነሳቱ ተገልጿል።
ከውይይቱ በኋላ በተለያዩ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ተይዘው የነበሩ የዘይት እና የስኳር ምርቶች እንዲለቀቁ ከውሳኔ ላይ ተደርሷል ተብሏል። በዚህም መሰረት የዘይት እና የስኳር ምርቶቹ ከነገ ጀምሮ ተለቅቀው ለገበያ እንደሚቀርቡ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)