በናሆም አየለ
ከፍትሕ ሚኒስቴር ህጋዊ የጥብቅና ፍቃድ ወስደው እየሰሩ ያሉ ጠበቆች፤ ዓመታዊ የግብር ክፍያቸውን ለመፈጸም ነጋዴዎች የሚይዙትን መዝገብ እንዲያቀርቡ በመጠየቃቸው ግዴታቸውን ለመወጣት መቸገራቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ገለጸ። ማህበሩ ይህን በማስመልከት ያቀረበውን ቅሬታ የተቀበለው የፍትሕ ሚኒስቴር፤ ጠበቆች በቀድሞው አሰራር እንዲስተናገዱ ገንዘብ ሚኒስቴርን ቢጠየቅም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
በ2013 ዓ.ም የተሻሻለው የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ፤ የማንኛውም የጥብቅና ድርጅት ወይንም ሸሪክ የግብር አከፋፈል፤ አግባብነት ባላቸው የሽርክና ማህበርን በተመለከቱ የግብር ህጎች እንደሚወሰን ይደነግጋል። ይህንን መሰረት በማድረግም፤ ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር የሚደረግ የጥብቅና አገልግሎት ውልን ይዘው ሲቀርቡ፤ በውሉ መሰረት ገቢያቸው ተሰልቶ ዓመታዊ ግብራቸውን እንዲከፍሉ ሲደረግ ቆይቷል።
ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ግን በዚህ የቁርጥ ክፍያ ምትክ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ የማህበሩ አባላት የሆኑ በተወሰኑ ጠበቆች ላይ አዲስ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሰለሞን እምሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አዲሱ አሰራር፤ ጠበቆች ነጋዴዎች የሚያቀርቡትን የሂሳብ መዝገብ አይነት፣ ከተመዘገበ ካፒታል ጋር እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ነው።
ከ5,400 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር፤ ጠበቆች በአዲሱ አሰራር የገጠማቸውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ጥናት ማድረጉን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። ማህበሩ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከገንዘብ ሚኒስቴር ካደረገው ውይይት በኋላ፤ ጠበቆች ግብር የሚከፍሉበት ልዩ መመሪያ እንዲዘጋጅ ከስምምነት ተደርሶ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ስምምነቱን ተከትሎም ከሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ እና ከማህበሩ የተውጣጡ አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ ተዋቅሮ፤ ከሚያዝያ 2016 ዓ.ም. መመሪያው ሲዘጋጅ መቆየቱን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል። ሆኖም የመንግስትን ገቢ በተመለከተ መመሪያ የማውጣት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር፤ መመሪያው እንዲቆይ በማዘዙ ሂደቱ መቆሙን የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አባል ገልጸዋል።
መመሪያው ተዘጋጅቶ እስኪያልቅ፤ ጠበቆች በቀድሞው የቁርጥ ክፍያ አሰራር እንዲስተናገዱ የገንዘብ ሚኒስቴር የተካተተበት የዝግጅት ኮሚቴ ከስምምነት ላይ ደርሶ እንደነበር አቶ ሰለሞን አብራርተዋል። ሆኖም የ2016ን በጀት ዓመት ግብር ለመክፈል ወደ አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሄዱ ጠበቆች፤ “የሂሳብ መዝገብ እና የተመዘገብ ካፒታል ጋር ካላቀረባችሁ አትስተናገዱም” በሚል መጉላላት እየደረሰባቸው እንደሆነ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለት ጠበቆችም፤ ግብር ለመክፈል በሄዱበት ወቅት ከደንበኞቻቸው ክፍያ የተቀበሉበትን የባንክ ማስረጃ ወይም ለተፈጸመ ክፍያ የሰጡትን ደረሰኝ እንዲያመጡ መጠየቃቸውን ገልጸዋል። የአገልግሎት ክፍያዎች ሁሌም በባንክ እንደማይፈጸሙ እና ለሰጠው አገልግሎት ለሚፈጸም ክፍያ ደረሰኝ የሚቆርጥ ጠበቃ “ቁጥሩ ትንሽ” መሆኑንም የሚያስረዱት ጠበቆቹ፤ በዚህም ምክንያት ክፍያ የተፈጸመበትን ማስረጃ ወይንም ደረሰኝ ሲጠይቁ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር በአባላቱ ላይ እየደረሰ ያለው ይህን መሰሉን መጉላላት በመጥቀስ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፤ ለችግሩ መፍትሔ እንዲበጅለት አቤቱታ አቅርቧል። የፍትሕ ሚኒስቴር የማህበሩን ቅሬታ በመቀበል ባለፈው አርብ ሐምሌ 26፤ 2016 ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፤ የጠበቆች የታክስ አከፋፈል በነባሩ አሰራር መሰረት እንዲቀጥል መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር በዚሁ ደብዳቤው፤ ከጠበቆች የግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን ችግር “በዘላቂነት ለመፍታት” ያስችላል ያለውን የመመሪያ ዝግጅትም አንስቷል። የመመሪያው ዝግጅት “በተቻለ ፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንዲገባ” እንዲደረግም ሚኒስቴሩ በደብዳቤው አሳስቧል።
ለእነዚህ ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስቴር ከሁለት ቀን በፊት ማክሰኞ ሐምሌ 30፣ 2016 በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚሁ ደብዳቤው፤ ጠበቆች በነባሩ አሰራር የግብር ክፍያቸውን እንዲያከናውኑ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። ሚኒስቴሩ ከአንድ ዓመት በፊት የጠበቆች የግብር አከፍፈል ምን መምሰል እንዳለበት በግልጽ ማስቀመጡን በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።
በዚሁ የገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ መሰረት፤ ጠበቆች “ያወጧቸው አስፈላጊ ወጪዎች በተቀናሽነት እንዲያዝላቸው ሆኖ” የግብር ግዴታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል። ይህ አሰራር ከ2016 ዓ.ም. የግብር ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በወቅቱ ተገልጾ እንደነበር በደብዳቤው ያስታወሰው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ጠበቆች “ለትክክለኛ የግብር አወሳሰን እና አከፍፈል የሚረዱ አግባብነት ያላቸውን የሂሳብ መዝገቦች በመያዝ” ግብር ሊከፍሉ እንደሚገባ አሳስቧል።
ጠበቆች በግብር አከፋፈል ላጋጠማቸው ችግር በገንዘብ ሚኒስቴር የተሰጠው ምላሽ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው ተተችቷል። በገንዘብ ሚኒስቴር “የተጻፈው ደብዳቤ አሳሳች ነው። ሂደት ላይ ያሉትን ስራዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም። ምናልባት በችኮላ ተዘጋጅቶ ይሆናል፤ አላውቅም” ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“የተጻፈው ደብዳቤ አሳሳች ነው። ሂደት ላይ ያሉትን ስራዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም። ምናልባት በችኮላ ተዘጋጅቶ ይሆናል፤ አላውቅም”
– አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት
ጠበቆች በተደጋጋሚ እያጋጠማቸው ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻለው፤ በዝግጅት ላይ ያለው የጠበቆች የግብር አከፋፈል መመሪያ ሲጠናቀቅ መሆኑን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል። የመመሪያው ዝግጅትን በተመለከተ ማህበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግሩን እንደሚቀጥልም አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)