በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት “በልዩ ሁኔታ” መስጠቱን አስታወቀ። ሆኖም ቦርዱ ህወሓት ያቀረበለትን “የቀድሞውን ህልውና ወደነበረበት የመመለስ” ጥያቄ አለመቀበሉን አስታውቋል።
ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ የህወሓትን ህጋዊ እውቅና የማግኘት ጉዳይ በተመለከተ ዛሬ አርብ ነሐሴ 3፤ 2016 ባወጣው መግለጫ ነው። ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓት “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን” እንዳረጋገጠ በመጥቀስ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት” የሰረዘው በጥር 2013 ዓ.ም ነበር።
ቦርዱ ለውሳኔ መነሻ አድርጎ የጠቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፤ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ባደረጉት የግጭት ማቆም ስምምነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ቆሟል። ይህንኑ ተከትሎ ህወሓት ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ቦርዱን በደብዳቤ ቢጠይቅም፤ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ጥያቄው “በህግ የተደገፈ ሆኖ አለመገኘቱን” በመጥቀስ ሳይቀበለው ቀርቷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር በምርጫ ቦርድ ለተነሳው የህግ ክፍተት ምላሽ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ በማዘጋጀት ባለፈው ግንቦት ወር በፓርላማ አጸድቋል። ሚኒስቴሩ ይህንኑ የአዋጅ ማሻሻያ በማጣቀስ፤ ህወሓት በ“ልዩ ሁኔታ” በፓለቲካ ፓርቲነት መመዝገብ እንዲችል ምርጫ ቦርድ “አስፈላጊውን ትብብር” እንዲያደርግ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቧል።
የሚኒስቴሩን ጥያቄ ተከትሎ ህወሓት የዛሬ ሁለት ሳምንት ሐምሌ 19፤ 2016 ለምርጫ ቦርድ ባስገባው ደብዳቤ፤ “የፓርቲው ህጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት እንዲመለስለት” ጥያቄ አቅርቧል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ፤ ህወሓት በድጋሚ ያቀረበለትን ይህን ጥያቄ አለመቀበሉን አስታውቋል።
ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅን በማስረጃነት በማቅረብ ነው። አዋጁ “በአመጽ ተግባር ተሰማርቶ ለተሰረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ህልውና መልሶ የሚሰጥ የህግ ድንጋጌ ያልያዘ መሆኑ” በምርጫ ቦርድ መግለጫ ተጠቅሷል።
“አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል”
– የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ማሻሻያ
ሆኖም የአዋጅ ማሻሻያው “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችል ድንጋጌን በውስጡ አካትቷል። “አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል አዋጁ ይደነግጋል።
ይህንኑ ማረጋገጫ ከፍትሕ ሚኒስቴር ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። ማረጋገጫውን ያገኙ የፓለቲካ ቡድኖች፤ ለምርጫ ቦርድ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው በአዋጅ ማሻሻያው የተጠቀሱ ሰነዶችንም ህወሓት ከማመልከቻው ጋር አያይዞ ማስገባቱንም ቦርዱ ገልጿል። ህወሓት ለቦርዱ ያቀረባቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲው ፕሮግራም፣ የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና ፊርማ የያዙ ሰነዶችን ነው።
እነዚህን ሰነዶች መሰረት በማድረግ “ህወሓት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ” መወሰኑን ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል። ለህወሓት የሚሰጠው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ “በልዩ ሁኔታ” የሚል ቃላት የተካተተበት እንደሆነም ቦርዱ ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ያወጣው እና የቦርዱን ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ፊርማ የያዘው የምስክር ወረቀትም ይህንኑ በጉልህ ይዟል። “ይህ የክልላዊ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ የምዝገባ እና ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ፤ ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ዛሬ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ተሰጥቶታል” ይላል።
ህወሓት በልዩ ሁኔታ የመመዝገቡን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ከደረሰው ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ፤ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግም ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ አስቀምጧል። “የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በተገኙበት” መደረግ እንዳለበት በተገለጸው በዚሁ ጉባኤ ላይ፤ ፓርቲው “መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጸድቅ” እና “አመራሮችን እንዲያስመርጥ” ምርጫ ቦርድ ውሳኔ አስተላልፏል።
ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን የቅድመ ጉባኤ ዝግጅት የተመለከቱ ስራዎችን ለመከታተል እንዲረዳው፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤው የሚያደርግበትን ዕለት ከ21 ቀናት በፊት አስቀድሞ ማሳወቅ እንዳለበትም ቦርዱ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል። ህወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከመተላለፉ አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ፤ ጠቅላላ ጉባኤውን በሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚያካሄድ አስታውቆ ነበር።
ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅቱን መቀጠሉን በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ቢያስታውቅም፤ ጉባኤው መቼ እንደሚካሄድ ግን እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፤ አስቀድሞ በታቀደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ በዛሬው ዕለት በተሰራጨ ደብዳቤያቸው አስታውቀው ነበር።
አቶ ጌታቸው ከጠቅላላ ጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉት፤ ሂደቱ “ዲሞክራሲያዊ እና ህጋዊ አይደለም” የሚል ምክንያት በማቅረብ ነው። ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ያስገባው የምዝገባ ጥያቄም “በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እውቅና የሌለው ነው” ሲሉ በደብዳቤያቸው ተችተዋል። አቶ ጌታቸው ይህን ደብዳቤያቸውን የላኩት ለህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና ለፓርቲው የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ነው።
የህወሓት የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ባወጣው መግለጫ፤ የፓርቲው ድርጅታዊ ጉባኤ አካል መሆን እንደማይፈልግ አስታውቆ ነበር። ድርጅታዊ ጉባኤው “‘የበላይነት አለኝ’ በሚል አካል ተጠልፎ አደገኛ አካሄድ ላይ መሆኑን” በወቅቱ የገለጸው የቁጥጥር ኮሚሽኑ፤ “የእዚህ አደገኛ አካሄድ አካል ላለመሆን” ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጾ ነበር።
በህወሓት ውስጥ ያለው ክፍፍል በይፋዊ መግለጫዎች በሚንጸባረቅበት በዚህ ወቅት፤ ስብሰባ ላይ የሰነበቱት የትግራይ ወታደራዊ አዛዦች “ከየትኛውም የፖለቲካ አሰላለፍ ነጻ እንደሚሆኑ” አስታውቀዋል። ወታደራዊ አዛዦቹ ትላንት ባወጡት መግለጫ “የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደማይታገሱ” አመልክተዋል።
በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ ሊከናወን እንደሚገባም ወታደራዊ አዛዦቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል። ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ህወሓት ከሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ፓርቲው “ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ” በቦርዱ ክትትል እንደሚደረግበት ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]