በሙሉጌታ በላይ
በሶማሌ ክልል፣ በሸበሌ ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች በተከሰተ የጎርፍ አደጋ፤ ሶስት ሺህ የሚጠጉ አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ መሐመድ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ለጎርፍ አደጋው መከሰት ምክንያት የሆነው የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሙላት እየጨመረ በመምጣቱ፤ የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ኃላፊው አስታውቀዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የሚነሳው የዋቢ ሸበሌ ወንዝ፤ በሶማሌ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ ሲያደርስ ቆይቷል። የዘንድሮው የዋቢ ሸበሌ ወንዝ የውሃ ሙላት የተከሰተው ከአንድ ሳምንት በፊት መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱልፈታ፤ ይህን ተከትሎም ሙስተሂል፣ ቀላፌ እና ፌር-ፌር በተባሉ ወረዳዎች የሚገኙ አካባቢዎች በጎርፍ መጥለቅለቃቸውን አስረድተዋል።
በዚህም ሳቢያ በሶስቱ ወረዳዎች የሚኖሩ 2,827 አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ምክትል የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት ተፈናቃዮቹን ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በመውሰድ በጤና ተቋማት እና በድንኳኖች ውስጥ እንዲጠለሉ ማድረጉን የገለጹት አቶ አብዱልፈታ፤ በአሁኑ ወቅትም የምግብ እና ሌሎች ድጋፎች እያደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
“በሶስት መኪና ምግብ እና ምግብ ነክ እርዳታ ነው የላክነው። ዱቄት፣ ፋፋ፣ በቆሎ፣ [ተፈናቃዮች] ውሃ የሚቀዱበት ጄሪካኖች እና ምንጣፍ ልከናል” ሲሉ የሶማሌ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ለተፈናቃዮቹ ያከፋፈለውን የዕለት ደራሽ እርዳታ አይነት ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል። ቢሮው ለእነዚህ ተፈናቃዮች እርዳታ ቢያዳርስም፤ የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሙላት እየጨመረ በመምጣቱ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ወንዙ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ በሙስተሂል፣ ቀላፌ እና ፌር-ፌር ወረዳዎች የሚገኝ 6,186 ሄክታር መሬት “በጎርፍ መሸፈኑን” የጠቆሙት አቶ አብዱልፈታ፤ በዚህ ምክንያት በመሬቱ ላይ ተዘርቶ የነበረ የበቆሎ እና የስንዴ ማሳ መውደሙን ገልጸዋል። በእነዚህ ወረዳዎች 22 የቁም ከብቶች በጎርፉ ተወስደው መሞታቸውንም ምክትል የቢሮ ኃላፊው አክለዋል።
የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ በሚያስተናግደው በሙስተሂል ወረዳ ያሉ አራት ትምህርት ቤቶች፣ አንድ ጤና ጣቢያ እና አንድ የእንስሳት ህክምና መስጫ ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ አብዱልፈታ ጨምረው ገልጸዋል። ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳቱ “ከፍተኛ የሚባል” እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ አብዱልፈታ፤ “ውሃ ውስጥ ገብቶ ንብረቶችን ነው ያበላሸው” ሲሉ የደረሰውን የአደጋ መጠን አስረድተዋል።
በሶማሌ ክልል ባለፈው አንድ ሳምንት በነበረው የጎርፍ መጥለቅለቅ እስካሁን የተጎዳ ሰው እንደሌለ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በክልሉ ባለፈው ጥቅምት እና ህዳር ወር በነበረው የዝናብ ወቅት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 33 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በወቅቱ በነበረው የጎርፍ አደጋ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ሲጠቁ፤ በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)