● ለአስር የክልሉ አመራሮችም “ማስጠንቀቂያ” ተሰጥቷቸዋል
በቤርሳቤህ ገብረ
በሲዳማ ክልል የፓርቲ እና የመንግስት ስራዎች አፈጻጸም ላይ የተደረገውን ግምገማ ተከትሎ፤ የክልሉ የገቢዎች ባለስልጣንን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ኃይሉ ጉዱራ ከስልጣናቸው ተነሱ። በግምገማው በክልሉ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ በተለያየ የኃላፊነት ቦታዎች የተመደቡ አራት አመራሮች ተመሳሳይ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
የ2016 ዓ.ም የሲዳማ ክልል የስራ አፈጻጸም ላይ የተደረገው ግምገማ፤ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲካሄድ ቆይቶ የተጠናቀቀው ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 9፤ 2016 ነው። በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ፤ የሲዳማ ክልል የ2017 በጀት ዓመት እቅድም ለውይይት ቀርቦ ነበር።
በስብሰባው ላይ ከሲዳማ ክልል የማዕከል መዋቅር፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ ከክልሉ አራቱም ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች መሳተፋቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገልጿል። በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ “በስነ ምግባር፣ በአቅም እና በአፈጻጸም” የተገመገሙ አመራሮች ላይ ውሳኔ መተላለፉን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈራ ቄንፋቶ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አመራሮቹ በተገኙበት በተላለፈው ውሳኔ፤ ስድስት በተለያየ ደረጃ ያሉ የስራ ኃላፊዎች ከስልጣን እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን 10 አመራሮች ደግሞ በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን አቶ ተፈራ አስረድተዋል። ከኃላፊነታቸው ከተነሱት አመራሮች መካከል የሲዳማ ክልል መንግስት ካቢኔ አባል የሆኑት አቶ ኃይሉ ጉዱራ ይገኙበታል።
አቶ ኃይሉ የሲዳማ ክልል የገቢዎች ባለስልጣንን በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙት፤ በመስከረም 2014 ዓ.ም. በተደረገው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ነበር። የክልል የገቢዎች ባለስልጣን፤ በ2016 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረው 13 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 76.7 በመቶ ብቻ ነው።
የበጀት ዓመቱ የስራ አፈጻጸም ግምገማ በተደረገበት የሀዋሳ ስብሰባ ላይ፤ አቶ ኃይሉ “ኃላፊነትን ባለመወጣት” እና “በስነ ምግባር ጉድለት” መገምገማቸውን በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኃላፊው ወደ ስልጣን በመጡበት በአጭር ጊዜ ውስጥ “ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተዋል” በሚል እንደተገመገሙም አስረድተዋል።
አቶ ኃይሉን ለግምገማ የዳረጋቸው በባለቤታቸው ስም የገዙት አንድ መኖሪያ ቤት መሆኑን እኚሁ የስብሰባው ተሳታፊ ተናግረዋል። የክልሉ የገቢዎች ባለስልጣንን የሚመሩት አቶ ኃይሉ፤ የሚከፍሉትን ግብርን ለማሳነስ የመኖሪያ ቤቱን ዋጋ “ከ13 ሚሊየን ብር ወደ 3.5 ሚሊየን ብር ዝቅ በማድረግ የውል ስምምነት አድርገዋል” የሚል ውንጀላ በስብሰባው ላይ እንደቀረበባቸው ምንጩ አመልክተዋል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ “ማጣራት ማድረግ እንደሚያስፈልግ” በመድረኩ ላይ መነሳቱንም የስብሰባው ተሳታፊ አክለዋል። አቶ ኃይሉ ለቀረበባቸው ውንጀላ በሰጡት ምላሽ “ቤቱን የገዛሁት ሰርቄ ሳይሆን የነበረኝን ቤት በባንክ አስይዤ ተበድሬ ነው” ብለዋል። ሆኖም ጉዳዩን በግምገማው ላይ ያነሱት ተሳታፊዎች፤ ኃላፊው ያላቸው ቤት “የተጠቀሰውን ያህል ብር ከባንክ ለመበደር የሚያበቃ አይደለም” በሚል መከራከራቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ተናግረዋል።
አቶ ኃይሉ ከባንክ ተበደርኩ ባሉበት ወቅት “ባንኮች ብድር እየሰጡ አልነበርም” የሚለውም ሌላ መከራከሪያ ሆኖ እንደቀረበባቸው ምንጩ ገልጸዋል። በሀዋሳው የግምገማ መድረክ በአቶ ኃይሉ ላይ የቀረበባቸው ሌላው ውንጀላ፤ ሽያጭ በተካሄደባቸው የቡና መፈልፈያ ሳይቶች “መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያጣ አድርገዋል” የሚል ነበር። ኃላፊው የሽያጭ ተመንን የተመለከቱ ውሳኔዎችን ይሰጡ የነበረው፤ “ያለ ባለሙያ ግምት መሆኑ” ለግምገማ እንዳበቃቸው የስብሰባው ተሳታፊ አመልክተዋል።
አቶ ኃይሉ የሚመሩት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች “ግብርን በአግባቡ እንዳይከፈል እያደረጉ” በመሆኑ እርምጃ እንዲወሰዱ ተጠይቀው አለማድረጋቸውም ኃላፊውን አስገምግሟቸዋል ተብሏል። ኃላፊው “በህጉ መሰረት እርምጃ የመውሰድ ስልጣን” እንዳላቸው የጠቀሱት ተሳታፊዎች፤ ይህን ባለማድረጋቸው “የመንግስት ሀብት እንዲባክን ምክንያት ሆነዋል” የሚል ውንጀላ አቅርበውባቸዋል።
አቶ ኃይሉ የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት አንደማይፈልጉ ገልጸዋል። በሀዋሳው የግምገማ መድረክ እንደ አቶ ኃይሉ ሁሉ፤ የሲዳማ ክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዋላና ዋኤን ጨምሮ በአራት አመራሮች ላይ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ውሳኔው ከተላለፈባቸው አመራሮች ውስጥ፤ በክልሉ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት እና የስምሪት ዘርፍን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ጴጥሮስ ማሩፋ አንዱ ናቸው። አቶ ጴጥሮስ “ስልጣናቸውን በመጠቀም” “የተሽከርካሪ ታርጋ እና የመንጃ ፈቃድ ሰጥተዋል” በሚል ተወንጅለዋል። በዚህ መልክ የሰጧቸው ታርጋዎች እና መንጃ ፈቃዶችም “ህጋዊ ላልሆኑ አላማዎች ውለዋል” የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል።
ኃላፊው ከዚህም በተጨማሪ “በሴት ተገልጋዮች ላይ ጾታዊ ትንኮሳ በማድረግ” ተገምግመው ከስልጣናቸው እንዲነሱ ውሳኔ መተላለፉን በሀዋሳው ስብሰባ የተሳተፉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ተናግረዋል። አቶ ጴጥሮስ ከሴት ተገልጋዮች ጋር በተገናኘ የቀረበባቸው ውንጀላ “መሰረት የሌለው፤ ውሸት ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተባብለዋል።
ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ያሉ ችግሮችንም ቢሆን፤ “አንድ ባለሙያ ጥፋት አንደሰራች ታውቆ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መቀመጡን” አስረድተዋል። ከሰሌዳ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ጥፋት የፈጸሙ ባለሙያዎች፤ “በዲሲፒሊን ጥሰት” እርምጃ እየተወሰደባቸው እና በህግም እየተጠየቁ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህ ረገድ የቀረቡት ውንጀላዎችም “ከእርሳቸው ጋር እንደማይገናኝ” በግምገማው ወቅት ምላሽ መስጠታቸውን አብራርተዋል።
ስምንት ቀናትን በፈጀው የፓርቲ እና የመንግስት ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ፤ ሌሎች 10 አመራሮች “በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን” የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገልጸዋል። በማስጠንቀቂያ ከታለፉት ውስጥ የሲዳማ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመው እንደሚገኙበት አቶ ተፈራ ጠቁመዋል።
በዚሁ የግምገማ መድረክ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፤ “በሌብነት እና በብልሹ አሰራር ውስጥ የገቡ አመራሮች” ሲሉ በጠሩዋቸው ኃላፊ ላይ “ፖለቲካዊ እርምጃ” መወሰዱን ተናግረዋል። በቀጣይም ተጨማሪ “ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወሰድም አስታውቀዋል ተብሏል።
የሲዳማ ክልል ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ መልኩ ባደረገው ግምገማ ላይ የሀዋሳ ከተማን በከንቲባነት ሲያስተዳድሩ በነበሩት አቶ ጸጋዬ ቱኬን ጨምሮ በ10 ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከስልጣን የማንሳት እርምጃ እንደወሰደ ይታወሳል። አቶ ጸጋዬ ከስልጣን የተነሱት በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” ተገምግመው እንደነበር አይዘነጋም።
ውሳኔው ከተላለፈባቸው በኋላ ወደ አሜሪካ የሄዱት አቶ ጸጋዬ፤ ወደ ሀገር ውስጥ ሲመለሱ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገው ክስ ተመስርቶባቸዋል። የተመሰረተባቸውን “ከባድ የሙስና ክስ” በእስር ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ጸጋዬ፤ ከስልጣን የተነሱበትን ውንጀላም ሆነ የቀረበባቸውን ክስ ሲያስተባብሉ ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)