ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የህወሓት ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ ተመረጡ

● ፓርቲው በጠቅላላ ጉባኤ ያልተሳተፉ አባላቱን አግዷል

በተስፋለም ወልደየስ

ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ ተመረጡ። አቶ አማኑኤል አሰፋ አቶ ጌታቸው ረዳን በመተካት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። 

ህወሓት ሁለቱን የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ያደረገው ላለፉት ስድስት ቀናት በመቐለ ከተማ ሲያደርገው የነበረውን አወዛጋቢ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ሲያጠናቅቅ ነው። በዛሬው የጉባኤ ውሎ፤ ዘጠኝ አባላት ያሉበት የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫም ተከናውኗል።

ፓርቲው ከስድስት ዓመት በፊት ባከናወነው ጉባኤ ከመረጣቸው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ በአሁኑ ምርጫ የተካተቱት ዶ/ር ደብረጽዮን፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር እና ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ብቻ ናቸው። ከጠቅላላ ጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ጌታቸው ረዳ እና አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 6 የፖሊት ቢሮ አባላት በአዲስ ተመራጮች ተተክተዋል።

የህወሓትን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተቀላቀሉት ውስጥ ያልተጠበቀውን ከፍተኛ ስልጣን ያገኙት፤ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፊት የትግራይ ክልል የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አማኑኤል አሰፋ ናቸው። አቶ አማኑኤል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። 

አዲሱ ምክትል ሊቀመንበር፤ ተቃውሞ እና ትችት ሲያስተናግድ የቆየው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ቃል አቃባይም ነበሩ። በዚሁ ጉባኤ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደማይሳተፉ አስቀድመው በይፋ አስታውቀው ነበር። 

እንደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሁሉ፤ የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትም ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም። ዛሬ ይፋ በተደረገው አዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ዝርዝር ውስጥ ከጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉት እነ አቶ ጌታቸው ረዳ አልተካተቱም። 

እነ አቶ ጌታቸው የጠቅላላ ጉባኤው ሂደት “ኢ-ዲሞክራሲያዊ” እና “የጥቂት ቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ነው” በሚል ተቃውሞ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፤ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ ግን ይህንን ውንጅላ  በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርግ ተደምጧል።

በዚሁ ጎራ አዘጋጅነት የተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ተነፍጎታል። በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ 783 ጉባኤተኞች መሳተፋቸው በዛሬው የመዝጊያ ስነ ስርአት ላይ ተገልጿል። ይህም በአጠቃላይ ከሚጠበቀው ጉባኤተኛ 82 በመቶውን የያዘ መሆኑ ተነግሯል።  

በዚሁ ስነስርአት ላይ በተነበበው የህወሓት የአቋም መግለጫ፤ ከድርጅታዊ ጉባኤ ራሱን ያገለለውን እና ጉባኤው እንዳይካሄድ “እንቅፋት ፈጥሯል” የተባለው ቡድን መታገዱ ተገልጿል። የቡድኑ አባላት “ጥያቄቸውን በጹሁፍ የሚያቀርቡ ከሆነ” ግን ወደ አባልነታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ፓርቲው ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)