በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን “የታጠቁ ኃይሎች” ባደረሱት ጥቃት፤ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 11 ሰዎች ተገደሉ

በሙሉጌታ በላይ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በኮንሶ ዞን፣ ሰገን ከተማ ባለፈው ቅዳሜ እና ከትላንት በስቲያ እሁድ በደረሰ ጥቃት፤ ስድስት ነዋሪዎች እና አምስት የፖሊስ አባላት መገደላቸውን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡርማሌ ኡጋንዴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ጥቃቱን ያደረሱት “የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች ናቸው” ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ወንጅለዋል።

በደራሼ ወረዳ ከምትገኝ ሀይቤና ከተባለች ቀበሌ እንደመጡ የተነገረላቸው የታጠቁ ኃይሎቹ፤ ወደ ሰገን ከተማ “በድንገት” የገቡት ቅዳሜ ነሐሴ 11፤ 2016 አመሻሽ ላይ መሆኑን አቶ ኡርማሌ ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ ወደ ከተማይቱ ከገቡ በኋላ “ከባድ ተኩስ” መክፈታቸውን የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፤ በመጀመሪያ ኢላማ ያደረጉት “የወረዳው የአስተዳደር እና የጸጥታ ተቋማት ላይ” እንደነበር አስረድተዋል። 

“ቀጥታ ተኩሱን የከፈቱት ወደ አስተዳደር እና ወደ ፖሊስ ጽህፈት ቤት፤ ፖሊስ ጣቢያው ላይ ነው። ከቅዳሜ ለሊት 6 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ሲታኮሱ ቆዩ። ከዚያ በኋላ በመሃል ረገብ አለ። ማለዳ ላይ 12 ሰዓት አካባቢ [በድጋሚ] ጀመሩ” ሲሉ አቶ አርማሉ በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ አብራርተዋል። ታጣቂዎቹን “በደንብ የተደራጁ” ሲሉ የገለጿቸው የሰገን ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ፤ በተኩስ ልውውጡ አምስት የፖሊስ አባላትን መግደላቸውን ተናግረዋል።

የሰገን ዙሪያ ወረዳ ታጣቂዎቹ “ተኩስ እንደከፈቱ”፤ ለኮንሶ ዞን እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሪፖርት ማድረጉን የሚገልጹት አቶ ኡርማሌ፤ ቅዳሜ ለሊት “የክልሉ አድማ በታኝ” የጸጥታ ኃይሎች ወደ ወረዳው መድረሳቸውን አመልክተዋል። ሆኖም ጥቃቱ ከጸጥታ ኃይሎች አቅም በላይ በመሆኑ፤ የፖሊስ እና የሚሊሺያ አባላት ከትላንት በስቲያ እሁድ ከተማይቱን ለቅቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ገልጸዋል።

የጸጥታ ኃይሎቹ ከተማይቱን ከለቀቁ በኋላ ታጣቂዎቹ ቤት ለቤት እየዞሩ ስድስት “ንጹሃንን ገድለዋል” ሲሉ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ወንጅለዋል። በታጣቂዎች የታገቱ እና እስካሁን ሁኔታቸውን ያልታወቀ የከተማይቱ ነዋሪዎች እንዳሉም ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ከፈጸሟቸው ግድያዎች እና እገታዎች በተጨማሪ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት “ማውደማቸውን” አቶ ኡርማሌ ጠቁመዋል።  

በታጣቂዎች “መዘረፋቸው” እና “መቃጠላቸው” ከተነገረላቸው የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሰገን ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ የከተማይቱ ፋይናንስ ቢሮ እና የከተማይቱ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ይገኙበታል። ታጣቂዎቹ የእነዚህ ተቋማት ንብረት የሆኑት “መኪናዎች እና ሞተር ሳይክሎችን ዘርፈው ወደ ሀይቤና [ቀበሌ] ወስደዋል” ሲሉ አቶ ኡርማሌ ከስሰዋል።

“ከደራሼ ወረዳ የመጡ ናቸው” የተባሉት “የታጠቁ ኃይሎች” እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ከተማውን ተቆጣጥረው በመቆየታቸው፤ የሟቾችን አስክሬን አንስቶ መቅበር አለመቻሉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል። የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ትላንት ሰኞ ከሰዓት በሰገን ከተማ አቅራቢያ ወደ ምትገኝ ቀበሌ ቢደርሱም፤ ወደ ሰገን ከተማ አለመግባታቸውን አቶ ኡርማሌ ተናግረዋል። 

“ታጣቂዎቹ እስካሁን ከተማ መሀል ላይ አሉ። የሰገን ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በሙሉ በጽንፈኞች ኃይል እጅ ላይ ነው ያለው። እኛም ሪፖርት እያደረግን፣ መንግስትም ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ፤ እስከዛሬ ቀጠናውን እና ህዝቡን ሰላም ያሳጡበት ሁኔታዎች አሉ” ሲሉ የታጠቁ ኃይሎች በአካባቢው በተደጋጋሚ እየፈጠሩ ያሉትን የጸጥታ ችግር አስረድተዋል። 

በአካባቢው የጸጥታ መድፍረስ በተደጋጋሚ መከሰት የጀመረው፤ በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር የነበረው “የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን” አደረጃጀት በ2011 ዓ.ም በአዋጅ ከፈረሰ በኋላ ነው። ይህንን ተከትሎም የሰገን ከተማ፣ በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ስር እንዲጠቃለል ተደርጓል።

ይህንን አደረጃጀት የሚቃወሙ “ጽንፈኛ ታጣቂ ኃይሎች” “ብሔርን መሰረት ያደረገ” ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አቶ ኡርማሌ ይናገራሉ። ጥቃቱ “የኮንሶ ተወላጆች ላይ” ያነጣጠረ መሆኑንም ያስረዳሉ። ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በህዳር 2013 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት፤ በሰገን ወረዳ ዙሪያ በደረሰ ጥቃት የ66 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 39 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጾ ነበር።

የአሁኑ ጥቃት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኮንሶ ዞን የመንግስት  ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ፤ “በጉዳዩ ላይ እየመከርን ነው። ስንጨርስ መረጃ እንሰጣለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።  የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያው ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ “ጽንፈኛ” እና “አሸባሪ” ሲል የጠራቸው ኃይሎች በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ በፈጸሙት ጥቃት “ንጹሃን” ሰዎች እና የፖሊስ አባላት መገደላቸውን አረጋግጧል። 

በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ግን መግለጫው አልጠቀሰም። “ጀግና የፖሊስ አባላትና ሲቪል አካላትን በመግደል የሚሳካ የጸረ ሰላም ኃይል ተልዕኮ እና አጀንዳ የለም” ያለው የዞኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፤ መንግስት “በጥፋት ኃይሎች” ላይ “ተመጣጣኝ እርምጃ” እንደሚወስድ አስታውቋል። የኮንሶ ዞን አስተዳደር “የወረዳውን ሰላም ለማስጠበቅ እና ሽፍቶችን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል”፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከፌዴራል መንግስት ጋር “በቅንጅት እየሰራ” መሆኑንም መምሪያው ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)