በናሆም አየለ
የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈልና የመሸጥ ስራን የሚሰራው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በዘረጋቸው መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ስርቆት ከ800 ሚልዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት ገለጸ። ተቋሙ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር፤ ተንቀሳቅሶ ስራን ለመስራት ተግዳሮት እንደሆነበት ገልጿል።
ይህ የተገለጸው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ትላንት ረቡዕ ነሐሴ 15፣ 2016 የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት በሰጡት መግለጫ ላይ ነው። ዋና ስራ አስፈጻሚው በዚሁ መግለጫቸው፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶቹ ላይ ስርቆት የተፈጸመው በ11 ክልሎች ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ስርቆቱ በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ውስጥ እንደሚደጋገም አቶ አሸብር ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 74 የኃይል አስተላላፊ ምሰሶዎች መውደቃቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ 54 ምሰሶዎች የወደቁት ብረቶቻቸው እየተፈቱ በመሰረቃቸው ምክንያት መሆኑም አብራርተዋል። በመሬት ናዳ ምክንያት የወደቁ የተወሰኑ ምሰሶዎች መኖራቸውንም አክለዋል።
በከፍተኛ ወጪ ከውጭ ሀገራት ተገዝተው መጥተው ኢትዮጵያዊ ባልሆኑ ተቋራጮች የተተከሉት ምሰሶዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት፤ መስሪያ ቤታቸው በበጀት ዓመቱ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አቶ አሸብር አስረድተዋል። ወጪው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ሊውል ይገባ እንደነበርም ጠቁመዋል።
በተቋማቸው ላይ ከሚቀርበው አቤቱታ ዋነኛው “የኃይል አቅርቦት ጥራት መውረድ” መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ መስሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ በሚያጋጥመው ስርቆት ምክንያት ግን ህብረተሰብ በሚፈልገው የጥራት ልክ ኃይል ማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት ከተመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 84 በመቶው ለሀገር ፍጆታ የዋለ መሆኑንም አመልክተዋል።
“በስርቆት ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጣችን ጥራቱ ቀንሷል። የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ሲወድቁ ለቀናት መብራት ይቋረጣል። አንድ ቦታ ሳይሆን፣ ብዙ ወረዳዎችን፣ ብዙ ክልሎችን ጨለማ ውስጥ ይከታል። በዚህም ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጣችን በሚፈለገው ደረጃ እየሆነ አይደለም” ሲሉ አቶ አሸብር ተቋሙ በዚህ ረገድ የገጠመውን ችግር አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)