በሙሉጌታ በላይ
የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከተፈጸመባት በኋላ የተገደለችውን ህጻን ሄቨን አወትን በተመለከተ፤ በዛሬው ዕለት ሲሰጥ የነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ በፖሊሶች እንዲቋረጥ መደረጉን የአይን እማኞች እና የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲቋረጥ የተደረገው፤ “ፍቃድ ያልተጠየቀበት ፕሮግራም ነው” በሚል ምክንያት ነው ተብሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ኢሊሌ ሆቴል የተዘጋጀውን ጋዜጣዊ መግለጫ እና የሻማ ማብራት መርሃ ግብር ያዘጋጁት፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) እና ዘመቻ በጾታዊ ጥቃት ኢትዮጵያ አባል ድርጅቶች በጋራ በመሆን ነው። መርሃ ግብሩ የተዘጋጀላት ህጻን ሄቨን የአስገድዶ መድፈር እና ግድያ የተፈጸመባት፤ በባህር ዳር ከተማ፤ ቀበሌ 14 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሐምሌ 25፤ 2015 ዓ.ም ነበር።
ወንጀሉን በተመለከተ ወላጅ እናቷ የሰጡት ቃለ ምልልስ በመገናኛ ብዙሃን ከተላለፈ በኋላ ጉዳዩ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ሰንብቷል። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ጉዳዩን በተመለከተ ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 14፤ 2016 ባወጣው መግለጫ፤ ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን አስታውቋል።
በህጻን ሄቨን ላይ የተፈፀመውን ወንጀል፤ “አሰቃቂ”፣ “ከማህበረሰቡ ባህል እና ወግ ያፈነገጠ” እና “ጸያፍ” ሲል የክልሉ ፍትሕ ቢሮ በመግለጫው አውግዞታል። የዛሬውን መርሃ ግብር ካዘጋጁት መካከል አንዱ የሆነው ኢሴማቅ፤ ወንጀሉ “ከአሰቃቂነቱ እና የህጻንዋን ህይወት እንዲያልፍ ከማድረጉ ባለፈ፤ በህጻናትና በሴቶች አካላዊ እና ስነልቦናዊ ደህነንት ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚያደርስ በመሆኑ ትኩረት የሚሻ” መሆኑን ገልጿል።
የማህበራት ቅንጅቱ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው ደብዳቤ ላይ፤ ዛሬ አርብ ነሐሴ 17፤ 2016 የተዘጋጀው መርሃ ግብር “በተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት” የተሰማቸውን ሀዘን ለመግለጽ እንዲሁም ለሟች ህጻን ቤተሰቦች ድጋፋቸውን ለማሳየት እንደሆነ አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ በወንጀል ፈጻሚው ላይ “ፍትህ እንዲሰፍን” በማሰብ፤ “የድርሻቸውን ለመወጣት” የዛሬውን መርሃ ግብር ማዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
ይህን አላማ በመያዝ የተጀመረው የዛሬው መርሃ ግብር አካል የሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ “ሲቪል በለበሱ ሰዎች እና ፖሊሶች” እንዲቋረጥ መደረጉን ሁለት የአይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በስፍራው የነበሩ አንድ ታዳሚ “ጋዜጣዊ መግለጫው መሃል ላይ ፖሊሶች ደርሰው አቁሙ ተባለ። ተሰብሳቢዎችን አስወጡ። ካሜራ የያዙትም ‘ፋይል አጥፍታችሁ ነው’ የምትሄዱት አሏቸው” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።
የዛሬው መርሃ ግብር እስከ 11 ሰዓት የሚቆይ እንደነበር የገለጹት ሌላ ታዳሚ፤ “ሲቪል የለበሰ ሰው” ወደ አዳራሹ ገብቶ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲቋረጥ ሲያዝ መመልከታቸውን ገልጸዋል። መግለጫው ከተቋረጠ በኋላ ፖሊሶች ታዳሚው እንዲወጣ ማድረጋቸውንም አክለዋል።
“ስድስተኛ ፎቅ ላይ ነበር መግለጫው የሚሰጠው። ከዚያ ላይ አስወረዱን። እታች ሆነን እየጠበቅን ነበር። ‘እዚህ መጠበቅ አይቻልም’ ተብሎ ወጣን። የኮንፍረንሱን አዘጋጆች ሰብስበው ሲያናግሯቸው ነበር” ሲሉ እኚሁ ታዳሚ የተመለከቱትን አስረድተዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የጋዜጣዊ መግለጫው አንድ አስተባባሪ፤ የፖሊስ አባላቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን ያቋረጡት “ፍቃድ ያልተጠየቀበት ፕሮግራም ነው” በሚል ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መግለጫዎችን “እንደዛሬው ሲያከናውኑ” እንደነበር የጠቆሙት አስተባባሪው፤ ሆኖም ይህን መሰል እክል ገጥሟቸው እንደማያውቅ አመልክተዋል።
“እኛ ከዚህ በፊትም ፕሮግራም ስናዘጋጅ ፍቃድ ጠይቀን አናውቅም። ይህ ሰልፍ አይደለም፤ የሆቴል ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ ደግሞ ተከፍሎበታል። መግለጫው ገና ተሰጥቶ ሳያልቅ ነው ያቋረጡት”
– የጋዜጣዊ መግለጫው አስተባባሪ
“እኛ ከዚህ በፊትም ፕሮግራም ስናዘጋጅ ፍቃድ ጠይቀን አናውቅም። ይህ ሰልፍ አይደለም፤ የሆቴል ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ ደግሞ ተከፍሎበታል። መግለጫው ገና ተሰጥቶ ሳያልቅ ነው ያቋረጡት” ሲሉ በዛሬው ዕለት የገጠማቸውን ሁኔታ አብራርተዋል። ጋዜጣዊ መግለጫውን ሊቀርጹ የመጡ የካሜራ ባለሙያዎች፤ የቀረጹትን እንዲያጠፉ በፖሊሶች መታዘዛቸውንም አክለዋል።
“የካሜራ ባለሙያዎች የቀረጹትን ነገር እንዳለ እንዲያጠፉ [ተደርገዋል]። አንድ ሰባት የሚሆኑ፣ ሲቀርጹ የነበሩ ካሜራዎች ነበሩ። ስልካቸው ላይ የቀረጹትን ነገር እንዲያጠፉ የተደረጉ ሰዎችም ነበሩ” ሲሉ የጋዜጣዊ መግለጫው አስተባባሪ ጨምረው ገልጸዋል።
ፖሊሶች የተወሰኑ የፕሮግራሙን አስተባባሪዎች ሰብስበው እዚያው ሆቴል ውስጥ ካናገራቸው በኋላ “ወደ የቤታቸው” እንዲሄዱ እንደፈቀዱላቸው ተናግረዋል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቃባይ አቶ ጄይላን አብዲ፤ ስለ ጉዳዩ “መረጃ የለኝም” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)