በሙሉጌታ በላይ
የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ ኃይሎች “የማስተናገድ ብሂሉን” እና “አካሔዱን” እንዲያቆም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አሳሰቡ። አምባሳደር ታዬ ይህን የተናገሩት፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ አርብ ነሐሴ 24፤ 2016 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የዛሬ መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል በተፈጠረው ውጥረት ላይ ያተኮረ ነበር። ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የባህር ወደብን ለማልማት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ መፈራረሟን ተከትሎ፤ የሶማሊያ መንግስት ጠንካራ ተቃውሞ ሲያሰማ ቆይቷል።
ታዬ በዛሬው መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በንግግር ለመፍታት የሚያስችል ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አሸማጋይነት ባለፈው ሰኔ እና ነሐሴ ወራት በአንካራ ከተማ ለሁለት ጊዜ ያህል ንግግር ቢያደርጉም፤ ውይይታቸው ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት ሶስተኛ ዙር ውይይት ለማድረግ ለመጪው መስከረም ወር ቀጠሮ ቢይዙም፤ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ በምትሰነዝረው ትችት እና በተጓዳኝ እየወሰደቻቸው ባለቻቸው እርምጃዎች ምክንያት በመካከላቸው ያለው ውጥረት ተባብሷል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ “የሶማሊያ መንግስት ተወካዮች ልዩነትን ማስፋት የአዘቦት ተግባራቸው አድርገውታል” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ወቅሰዋል።
ሶማሊያ እንደ ሀገር ትቆም ዘንድ “ኢትዮጵያ ብዙ መስዋትነትን መክፈሏን” የገለጹት ታዬ፤ ይህ አስተዋጽኦ በሶማሊያ ዘንድ “ከቁብ አልተቆጠረም” ብለዋል። የሶማሊያ መንግስት ተወካዮች “የመከላከያ ሰራዊት ያደረገውን ተጋድሎ ማንኳሰስ የንግግራቸው ማዕከል” እያደረጉት ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ታዬ ከዚህም በተጨማሪ ሶማሊያ አካባቢው ሰላም እንዲሆን ከማይፈልጉ አካሎች ጋር “እንቅስቃሴ እያደረገች ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ነሐሴ 22፤ 2016 ባወጣው መግለጫ፤ የሶማሊያ መንግስት “ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ ኃይሎች ጋር እየሰራ ነው” ሲል ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቆ ነበር።
ሚኒስቴሩ በዚሁ መግለጫው፤ “ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም” ሲል አስጠንቅቆ ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ በዛሬ መግለጫቸው ጉዳዩ “እንዲሁ በአዘቦት የሚታለፍ” አለመሆኑን በማንሳት የመስሪያ ቤታቸውን አቋም አስተጋብተዋል።
ኢትዮጵያ በስም ላልጠቀሰቻቸው ኃይሎች ጠንካራ መልዕክት ብታስተላልፍም፤ ከሶማሊያ ጋር ያላትን አለመግባባት ለመፍታት ግን አሁንም “የሰላም አማራጭን” መከተል አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች። “በሌሎች ደጋፊነት የመታበይ ስሜት ካለ፤ ያ መታበይ እስኪተነፍስ ድረስ የትዕግስት እና የሰላም ጥረታችን የሚቀጥል ይሆናል። ለእኛ የሚበጀን በአካባቢያችን ሰላምን ማጠንከር በመሆኑ በተቻለን መጠን ሁሉንም እንደርጋለን” ብለዋል ታዬ በዛሬው መግለጫቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)