በናሆም አየለ
እስካለፈው ወር መጨረሻ ድረስ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዋና ጸሀፊ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ እና የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጊደና መድኅን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢህአፓ) ተቀላቀሉ። ሌሎች ሁለት ፖለቲከኞችም ከአንድ ሳምንት በፊት ፓርቲውን መቀላቀላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
ኢዜማ ከተመሰረተበት ከግንቦት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና ጸሀፊነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አበበ፤ ከፓርቲው መልቀቃቸውን ያስታወቁት ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ነው። አቶ አበበ ከአዜማ የለቀቁት “ከፓርቲው አቋም እና አካሄድ ጋር ባለመስማማታቸው” እንደሆነ በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰው ነበር።
አቶ አበበን ጨምሮ አራት ፖለቲከኞች ከ10 ቀን በፊት በይፋ ኢህአፓን መቀላቀላቸውን የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ መላኩ ካሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አበበ፤ “ምንም ጥርጥር የለውም፤ ከኢትዮጵያ ፓለቲካ አልወጣም። የምቀላቀልበትን ፓርቲ ግን ጊዜው ሲደርስ እናገራለሁ” ሲሉ በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል።
የቀድሞው የኢዜማ ዋና ጸሀፊ ወደ ኢህአፓ መግባታቸውን ማረጋገጫ ባይሰጡም፤ አቶ አበበ የፓርቲው አባል ለመሆን የሞሉትን ፎርም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተመልክታለች። የአባልነት ፎርሙ አቶ አበበ ለቀድሞ ፓርቲያቸው መልቀቂያ ባስገቡት ዕለት ኢህአፓን መቀላቀላቸውን ያሳያል። አቶ አበበ ይህን አካሄድ የተከተሉት ኢዜማን በይፋ ሳይሰናበቱ በፊትም ቢሆን ኢህአፓን ለመቀላቀል ያስቡ ስለነበር እንደሆነ የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አብርሀም ሃይማኖት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
አቶ አበበ በሰኔ 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የፓርቲው አመራር ምርጫ፤ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ስብስብ አካል በመሆን በያዙት የዋና ጸሀፊነት የኃላፊነት ቦታቸው እንዲቀጥሉ በድጋሚ መመረጣቸው ይታወሳል። የዚህ ስብስብ ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት የኢዜማ ምክትል መሪ የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ እና የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ከፓርቲው ጋር መለያየታቸው አይዘነጋም።
በተመሳሳይ መልኩ ከኢዜማ በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ካስታወቁት መካከል የፓርቲው መስራች አባል የነበሩት አቶ ናትናኤል መኮንን ይገኙበታል። አቶ ናትናኤል “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ቃል ባለፈው ህዳር ወር በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ካስተባበሩት ፖለቲከኞች ውስጥ አንዱ ነበሩ።
በሰልፉ አስተባባሪነት የነበራቸው ሚና አቶ ናትናኤልን ለሶስት ወራት እስር ቢዳርጋቸውም፤ ለሰልፉ ድጋፍ ሲሰጥ የቆየውን ኢህአፓን “አሁናዊ አቋም” ይበልጥ እንዲያውቁ እድል ፈጥሮላቸዋል። ኢዜማ “በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለሚደርሰው መከራ ድምጽ መሆን ባለመቻሉ” ፓርቲውን እንደለቀቁ የሚያስታውሱት አቶ ናትናኤል፤ ኢህአፓ በአንጻሩ “ባለፉት አመታት ለህዝብ ድምጽ በመሆኑ” አንጋፋውን ፓርቲ ለመቀላቀል መወሰናቸውን ያስረዳሉ።
የቀድሞው የኢዜማ አባል “ከፓርቲው አመራሮች በቀረበላቸው ግብዣ” አማካኝነት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ኢህአፓን መቀላቀላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ከኢህአፓ ጋር “በፓለቲካ መድረኩ ላይ የተለየ ነገር እንሰራለን ብዬ አምናለሁ” ሲሉም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
እንደ እርሳቸው ሁሉ በህዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ በአስተባባሪነት ተሳትፈው ለወራት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ጊደና መድኅንም፤ “የዜግነት ፖለቲካን የሚያራምድ ነው” ያሉትን ኢህአፓን ተቀላቅለዋል። የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጊደና፤ ኢህአፓን ለመቀላቀል እንዲወስኑ ያደረጋቸው “ማንኛውም ግለሰብ በብሄር ማንነቱ ሳይሆን በፖለቲካዊ ብስለቱ ተመዝኖ ወደ አመራርነት የሚወጣበት በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አቶ ጊደና፤ ኢህአፓ “ለትግራይ ህዝብ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ” እንዲሆን ከፓርቲው አመራሮች ጋር በጋራ የመስራት እቅድ አላቸው። በትግራይ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የቆዩት ሌላኛው ፖለቲከኛ አቶ ይሳቅ ወልዳይ በበኩላቸው፤ ኢህአፓን ለመቀላቀል የወሰኑት “በፖለቲካ ትግል ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ የሚያስችላቸውን ነጻነት የሚሰጣቸው ሀገራዊ ፓርቲ ስለሆነ ነው” ይላሉ።
“ፈንቅል” የተሰኘውን የትግራይ ወጣቶች እንቅስቃሴን በመምራት እና በማስተባበር የሚታወቁት አቶ ይሳቅ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል ከአዲሱ ፓርቲያቸው ጋር ለመታገል አቅደዋል። አቶ ይሳቅ እነዚህ ችግሮች የሚቀረፉት “አራት ኪሎ ያለው ችግር ሲስተካከል ነው” የሚል እምነት አላቸው።
አቶ ይሳቅ እና ሌሎቹ ፖለቲከኞች ወደ ኢህአፓ የገቡት የሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም እና የሚያራምዳቸውን አቋሞች ተንተርሰው እንደሆነ ቢገልጹም፤ የቀድሞው የፓርቲው ዋና ጸሀፊ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁን ግን “ኢህአፓ በማኒፌስቶው ላይ የገለጻቸውን እና ያነገባቸውን ግቦች ወደ ተግባር ለማምጣት ይቸግረዋል” ባይ ናቸው።
ወ/ሮ ደስታ 50 አመት የተሻገረ ዕድሜ ያለውን ፓርቲ “የሚያዘምኑ” የሚሏቸውን ሃሳቦች ቢያቀርቡም፤ “ሰሚ ማጣታቸውን” ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ ገልጸው ነበር። ዋና ጸሀፊዋ በዚሁ ወቅት ለፓርቲው ደብዳቤው ባስገቡት ደብዳቤ፤ ከሐምሌ 1፤ 2016 ጀምሮ ከፓርቲው አባልነት በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)