የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ እና በአስመራ መካከል የሚያደርጋቸውን በረራዎች ከነገ ማክሰኞ ነሐሴ 28፤ 2016 ጀምሮ እንደሚያቋርጥ አስታወቀ። አየር መንገዱ በረራዎቹን ለማቋረጥ የተገደደው፤ በኤርትራ ባጋጠሙት “ከቁጥጥሩ ውጭ የሆኑ” “በጣም አስቸጋሪ የስራ ሁኔታዎች” ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን የገለጸው፤ ዛሬ ሰኞ ምሽት በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ባወጣው ማስታወቂያ ነው። አየር መንገዱ በዚሁ ማስታወቂያው፤ በውሳኔው የሚጎዱ ተጓዦች “ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ” በሌሎች አየር መንገዶች እንዲጓዙ ለማድረግ “የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ” ብሏል።
ለጉዞ የከፈሉትን ገንዘብ መውሰድ ለሚፈልጉ መንገደኞች፤ የትኬት ዋጋውን መጠን ተመላሽ እንደሚያደርግም አየር መንገዱ በተጨማሪ አማራጭነት አስቀምጧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዛሬውን ውሳኔ ይፋ ከማድረጉ በፊት፤ በአዲስ አበባ እና በአስመራ ከተማዎች መካከል ከሰኞ እና ማክሰኞ በስተቀር በሳምንት ለአምስት ቀናት በረራዎች ነበሩት።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካካሄዱት ጦርነት በኋላ ለሁለት አስርት አመታት በመካከላቸው ተቋርጦ የነበረውን የአየር በረራ ግንኙነት ያስጀመሩት ከስድስት አመት በፊት ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን የንግድ በረራ መልሶ ከጀመረበት ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካለፈው ወር ድረስ ያለመስተጓጎል ቀጥሎ ቆይቷል።
ባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባወጣው ማስታወቂያ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርጋቸው በረራዎች ከመጪው መስከረም 20፤ 2017 በኋላ እንደሚቋረጡ መግለጹ አይዘነጋም። የሀገሪቱ የሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት ይህን እርምጃ ለመውሰድ “የተገደደው”፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በተደራጀ እና ስልታዊ ዘዴዎችን” በተከተለ መንገድ “እየፈጸማቸው ነው” ባላቸው ድርጊቶች ምክንያት እንደሆነ በወቅቱ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በባለስልጣኑ ከተወነጀለባቸው ድርጊቶች መካከል፤ “የመንገደኞች ሻንጣ ስርቆት፣ ዘረፋ እና ጉዳት”፣ በበረራዎች ላይ የሚፈጠሩ “የተራዘሙ መዘግየቶች” እንዲሁም “አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ” የሚሉት ይገኙበታል። ሆኖም አየር መንገዱ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ውሳኔን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ ለበረራ እግዱ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች እንዳልተገለጹለት አስታውቆ ነበር።
በጉዳዩ ላይ ግልጽ መረጃ ለማግኘት ከሀገሪቱ የሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚሁ መግለጫው አመልክቷል። በመስሪያ ቤቱ በኩል የሚነሱ “ማናቸውንም ጉዳዮች”፤ “በወዳጅነት መንፈስ” እና “በፈጠነ መልኩ” ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑንም አየር መንገዱ በወቅቱ መግለጹም ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]