ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከቀጣዩ አመት ጀምሮ የስራ እና ተግባር ትምህርቶች ሊሰጥ ነው

በቤርሳቤህ ገብረ

ከቀጣዩ ዓመት የትምህርት ዘመን ጀምሮ ለ11ኛ ክፍል ተማሪዎች፤ የስራ እና ተግባር የሙያ ትምህርቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ሊጀምር ነው። ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሚሰጡ ትምህርቶች የሚሆኑ “ሞጁሎች” በቀጣይነት እንደሚዘጋጁም ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሰጥ የታቀደው የስራ እና ተግባር ትምህርት፤ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲን መሰረት ያደረገ ነው። ፖሊሲው የስራ እና ተግባር ትምህርቶች፤ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ከእድሜያቸው ጋር በተመጣጠነ መልኩ እንዲሰጡ ማዕቀፎችን አስቀምጧል።

ፖሊሲውን ተንተርሶ የተዘጋጀው ስርዓተ ትምህርት፤ የስራ እና የተግባር ትምህርት ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጠው አንድ የትምህርት አይነት እንደሆነ አመልክቷል። የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በበኩላቸው፤ ከ40 የሙያ እና ተግባር ትምህርቶች ውስጥ አንዱን መርጠው እንዲማሩ እንደሚደረግ በስርዓተ ትምህርቱ ማዕቀፍ ላይ ተካትቷል።

በ2017 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ለ11ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጡት የስራ እና ተግባር ትምህርቶች ብዛት 12 ብቻ መሆናቸውን በትምህርት ሚኒስቴር የስራ እና ተግባር የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ አቶ ግርማ ደምሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሰባት የስራ እና የተግባር ትምህርቶችን የሚያማርጡ ሲሆን ለማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ አምስት ትምህርቶች በተመሳሳይ መልኩ ቀርበውላቸዋል።

ለተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰጡ ትምህርቶች፤ የድረ ገጽ-ንድፍ እና ልማት፣ የኮምፒውተር ጥገና እና አውታረ መረብ መሆናቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በግብርና ሳይንስ ዘርፍ ለእነዚሁ ተማሪዎች የቀረቡት ትምህርቶች፤ የእንስሳት እርባታ እና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ሲሆኑ ቀሪዎቹ የእንጨት ስራ ቴክኖሎጂ፣ የህንጻ ማጠናቀቂያ ስራ እና የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት ትምህርቶች ናቸው። 

በቀጣዩ አመት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንደ ምርጫቸው እንዲማሩ ከቀረቡ የትምህርት ዝርዝሮች ውስጥ የሂሳብ አያያዝ እና ፋይናንስ እንዲሁም የግብይት እና የሽያጭ አስተዳደር ይገኙበታል። ለማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በአማራጭነት የቀረቡት ሌሎች የስራ እና ተግባር ትምህርቶች፤ የማህበራዊ እና የሥነ ልቦና ክብካቤ (psycological caregiving)፣ የድምጽ ጥበብ (voval performance) እና ጋዜጠኝነት ናቸው። 

የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ከቀለም ትምህርቶቻቸው በተጓዳኝ የሚመርጡትን የስራ እና የተግባር ትምህርት በሳምንት 10 ክፍለ ጊዜ እንደሚማሩ አቶ ግርማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ተማሪዎቹ የመረጡትን የስራ እና የተግባር ትምህርት በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ማሳደግ ከፈለጉ እስከ ደረጃ ስምንት እና የዶክትሬት ዲግሪ ድረስ መማር እንደሚችሉም የስርዓተ ትምህርት ባለሙያው ጠቁመዋል።

የስራ እና የተግባር ትምህርቶችን በ2017 የትምህርት ዘመን ለመስጠት የሚያስፈልጉ መምህራንን ለመቅጠር የተዘጋጁ መስፈርቶችን ለክልል እና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ከአራት ወራት በፊት መላኩን አቶ ግርማ ገልጸዋል። ይህንን መሰረት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራን ቅጥር ማስታወቂያ ባለፈው ሳምንት አውጥቷል። 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ፓን ኔሽን አካዳሚ፤ በተመሳሳይ መልኩ በሶስት የሙያ ዘርፎች ትምህርቶችን የሚሰጡ መምህራንን ለመቅጠር በሂደት ላይ መሆኑን የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ሙላት አለም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በትምህርት ቤታቸው የሚማሩ ተማሪዎች፤ መማር የሚፈልጓቸውን የስራ እና የተግባር ትምህርት አይነት መርጠው የጨረሱት ከሰባት ወራት በፊት እንደነበር አቶ ሙላት ገልጸዋል። 

ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ያሉት ፓን ኔሽን አካዳሚ፤ በቀጣዩ ዓመት ለመስጠት የተዘጋጀው የተወሰኑ የስራ እና የተግባር ትምህርቶችን ብቻ ነው። ትምህርት ቤቱ በእነዚህ የትምህርት አይነቶች ብቻ የተወሰነው፤ እንደ ከብት እርባታ አይነት ትምህርቶች በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ምክትል ርዕሰ መምህሩ አስረድተዋል።   

የትምህርት ሚኒስቴር የስራ እና የተግባር የስርዓተ ትምህርት ባለሙያው አቶ ግርማ፤ ትምህርት ቤቶች በአየካባቢያቸው ያለውን ጸጋ ታሳቢ በማድረግ የሙያ አይነቶችን መርጠው መስጠት ይችላሉ ብለዋል። ነገር ግን ትምህርቱን ሙሉ ለሙሉ አለመስጠት እንደማይቻል ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)