በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች ለኢሬቻ በዓል እንግዶች እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ሊያደርጉ ነው

በቤርሳቤህ ገብረ

በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ የሚከበረውን ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል ለሚታደሙ እንግዶች፤ በከተማይቱ የሚገኙ ሆቴሎች እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ሊያደርጉ ነው። የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ለበዓሉ ቅናሽ የሚያደርጉ ሆቴሎች ዝርዝር እንዲገለጽለት ባለፈው ሳምንት ጥያቄ ማቅረቡም ተነግሯል። 

ቢሮው ጥያቄውን ያቀረበው 170 ሆቴሎችን በአባልነት ለያዘው የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር መሆኑን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህንኑ ተከትሎ ማህበሩ ለአባላቱ ለኢሬቻ በዓል ቅናሽ እንዲያደርጉ መልዕክት ማስተላለፉን ገልጸዋል።

በበዓላት ወቅት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንግዶችን ታሳቢ በማድረግ ሆቴሎች ቅናሽ ማድረጋቸው የተለመደ መሆኑን የሚያስረዱት ወ/ሮ አስቴር፤ ለኢሬቻ በዓል የታቀደው ቅናሽም “እንደግዴታ የቀረበ” አለመሆኑን አብራርተዋል። ማህበሩ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ የተወሰኑ ሆቴሎች ቅናሹን “በፓኬጅ ማዘጋጀታቸውን” ማስታወቃቸውንም አክለዋል። 

በዚህ መልኩ ቅናሽ የሚያደርጉ ሆቴሎች፤ ለእንግዶቻቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ጭምር ለማቅረብ እንዳቀዱ ማስታወቃቸውን ወ/ሮ አስቴር አመልክተዋል። ቀሪዎቹ ሆቴሎች ደግሞ በመኝታ ክፍሎቻቸው ላይ ብቻ ቅናሽ እንደሚያደርጉ ለማህበሩ እንደገለጹ አስታውቀዋል። 

የኦሮሞ ህዝብ የክረምቱን ወቅት በሰላም ላሳለፈው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት እና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለምንበት የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ በይፋ መከበር የጀመረው ከ2012 ዓ.ም. ወዲህ ነው። በዓሉ በመዲናይቱ ላለፉት አራት ዓመታት በዋነኛነት የተከበረው መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው “ሆራ ፊንፊኔ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው።

የኢሬቻ በዓል ለረጅም ዓመታት ሲከበር በቆየበት በቢሾፍቱ “ሆራ አርሰዴ” የሚካሄደው፤ ከአዲስ አበባው መርሃ ግብር ማግስት በመጪው እሁድ መስከረም 26፤ 2017 እንደሚሆን የአባ ገዳዎች ህብረት ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)