በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን፤ አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ማንሳቱን አስታወቀ

በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ማንሳቱን አስታወቀ። የጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት የካቢኔ አባላትን ጨምሮ 13 ኃላፊዎችን በተመሳሳይ መልኩ ከኃላፊነት ማውረዱን የገለጸው ቡድኑ፤ በምትኩ ተተኪ አመራሮችን መሾሙን ይፋ አድርጓል። 

የእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 በይፋዊ የህወሓት የፌስቡክ ገጽ ባሰራጨው መግለጫ ነው። ህወሓትን ወክለው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በክልሉ ዞኖች በአመራርነት የተመደቡ ኃላፊዎች እንዲነሱ ውሳኔ የተላለፈው፤ በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው አርብ ባካሄደው ስብሰባ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል።

ይህን ውሳኔ ያሳለፈው 45 አባላት ያሉበት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተመረጠው፤ ባለፈው ነሐሴ ወር መጀመሪያ በተካሄደ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ካልሰጠው ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ፤ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል። 

እነ አቶ ጌታቸውም ሆነ የቁጥጥር ኮሚሽኑ አባላት፤ የጠቅላላ ጉባኤው ሂደት “ኢ-ዲሞክራሲያዊ” እና “የጥቂት ቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ነው” በሚል ምክንያት ነበር በጉባኤው ሳይሳተፉ የቀሩት። ሆኖም በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን 14ኛ የድርጅት ጉባኤውን አካሄዶ፤ አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን መርጧል። 

ይኸው ቡድን በጉባኤው ያልተሳተፉ አባላትን ከፓርቲ አባልነት ማገዱን ካስታወቀ ከሳምንታት በኋላ ሙሉ በሙሉ ከፓርቲው ማሰናበቱን አስታውቆ ነበር። የእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ባለፈው መስከረም ወር ባወጣው መግለጫ፤ ክህወሓት የተሰናበቱት አባላት “በፓርቲው ስም የሚደረጉ ማንኛውንም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንዳያደርጉ” አስጠንቅቆ ነበር።  

ሆኖም በአቶ ጌታቸው የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች እና በጠቅላላ ጉባኤ ያልተሳተፉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ጎራ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “ይህ ቡድን በኃላፊነት ላይ በቆየ እና ተጨማሪ ዕድል ባገኘ ቁጥር ሌላ መዘዝ እና ብሔራዊ ጥፋት የሚያመጣ መሆኑ ግልጽ ነው” ሲል ወንጅሏል።

በዚህም ምክንያት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ፤ በህወሓት ስም አስተዳደራዊ ኃላፊነት የያዙ አመራሮች ወርደው በምትኩ ሌሎች የፓርቲው ተወካዮች እንዲተኩ ውሳኔ መተላለፉን በመግለጫው ሰፍሯል። በውሳኔው መሰረትም፤ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በፕሬዝዳትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ጌታቸው ረዳ ከዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 ጀምሮ “ከተሰጣቸው ኃላፊነት የወረዱ መሆኑን” መግለጫው አትቷል። 

የአቶ ጌታቸው ከስልጣን መሻር “ከፌደራል መንግስት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመግባባት የሚፈጸም” መሆኑንም በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን አስታውቋል። አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በርዕሰ መስተዳድርነት እንዲሾሙ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት በመጋቢት 14፤ 2015 ነበር።

የፌደራል መንግስት ሹመቱን የሰጠው፤ የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደርን የሚያቋቋም ደንብ በዚሁ ዕለት ካጸደቀ በኋላ ነው። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን ማቋቋም ያስፈለገው፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ባደረጉት የሰላም ስምምነት መሰረት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። 

የትግራይ ክልልን አስፈጻሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት የተጣለባቸው አቶ ጌታቸው፤ ከሹመታቸው ሁለት ሳምንት በኋላ 27 አባላት ያሉበትን ካቢኔ አቋቁመው ወደ ስራ ገብተዋል። በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን በዛሬው መግለጫው፤ በአቶ ጌታቸው ካቢኔ ውስጥ ከተካተቱ አባላት ውስጥ አራቱ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን አስታውቋል። 

ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ በመግለጫው ከተዘርዘሩ የካቢኔ አባላት ውስጥ የህወሓት ነባር ታጋይ የሆኑት አቶ በየነ ምክሩ ይገኙበታል። ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት፣ ዶ/ር ሓጎስ ጎደፋይ እና ወ/ሮ አልማዝ ገብረጻድቅ በመግለጫው የተጠቀሱ የካቢኔ አባላት ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]