በአማራ ክልል “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ” የሚፈጸሙ እስሮች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ኢሰመኮ አሳሰበ

በሙሉጌታ በላይ

በአማራ ክልል በበባህር ዳር፣ ጎንደር ከተሞች እና በተለያዩ አካባቢዎች ከመስከረም ወር አጋማሽ  ጀምሮ “በአዲስ መልክ” በርካታ ሰዎች “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ” እየታሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በክልሉ እየተካሄዱ ያሉት የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን እና መርሆችን “ያልተከተሉ” እስሮች በአፋጣኝ እንዲቆሙም አሳስቧል።

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው ዛሬ እሁድ መስከረም 26፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ኢሰመኮ በዚህ መግለጫው፤ “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ” እስር ተፈጽሞባቸዋል ካላቸው ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሚዲያ እና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ይገኙባቸዋል። 

ለእስራት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል “ቋሚ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው” እንደሚገኙበት ኮሚሽኑ ገልጿል። እስረኞቹ የዛሬው መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ “ፍርድ ቤት ያልቀረቡ” መሆናቸውንም አመልክቷል።

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ በትጥቅ ግጭት እና በጸጥታ መደፍረስ ወቅትም ቢሆን ሲቪል ሰዎችን ለመያዝ እና በወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ “በቂ ህጋዊ ምክንያት መኖሩን ማረጋገጥ” እንደሚገባ ተናግረዋል። “የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በፍርድ ቤት የተሰጠ የመያዣ እና የብርበራ ትእዛዝ” ሊኖር እንደሚገባም ራኬብ አስገዝንበዋል።

በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች “በመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ብቻ” እና “መብቶቻቸውን ባከበረ ሁኔታ መያዛቸው ሊረጋገጥ” እንደሚገባ የጠቆሙት ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነሯ፤ ተጠርጣሪዎቹ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። ይህንን ባላከበረ መልኩ በአማራ ክልል የሚፈጸሙት እስሮች፤ በታሳሪዎች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ “አሉታዊ” የሆነ ስነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጽእኖ እንደሚኖራቸውም ራኬብ ተናግረዋል። 

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በአማራ ክልል ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ፤ የሚመለከታቸውን የክልሉን የአስተዳደር እና ጸጥታ አካላት ለማነጋገር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል  በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።  ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው “የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን እና መርሆዎችን ያልተከተሉ እስሮች በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል”ብሏል። 

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርቦ ነበር። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚሁ መግለጫው በአማራ ክልል የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በዘመቻ በሚፈጽሙት እስር፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን አስታውቆ ነበር። 

ለእስር ከተዳረጉት ውስጥ አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት እና በሌሎችም ህጎች በተደነገገው መሰረት “በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም” የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም። የአማራ ክልል በዚሁ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ለክልሉ ህዝብ ሰላምን ለማስፈን ከሰሞኑ በተወሰደ እርምጃ “በእገታ እና ዘረፋ የተሰማሩ”፣ በከተማ ሆነው “የማስተባበር” ስራ የሚያከናወኑ፣ ለ“ጽንፈኛ” ኃይሎች “የሎጀስቲክ እና የመረጃ ምንጮች” በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)