በሙሉጌታ በላይ
ላለፉት ስምንት ወራት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፤ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ። የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ፤ የአቶ ታዬን ሹመት በአምስት ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቀዋል።
አቶ ታዬ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት፤ የስራ ዘመናቸው በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ የሚጠናቀቀውን ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ተክተው ነው። በኢፌዲሪ ህገ መንግስት “ለፕሬዝዳንትነት እጩ የማቅረብ ስልጣን” የተሰጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ ታዬን ለፕሬዝዳንትነት እንዲቀርቡ “የወሰነው” ቅድሚያ “ዝግ ስብሰባ” ካደረገ በኋላ ነው።
ለጋዜጠኞች አስቀድሞ በተላከው የመርሃ ግብር ማሳወቂያ ላይ የዛሬው የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ስብሰባ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ የተገለጸ ቢሆንም፤ በሰዓቱ በስፍራው የተገኙት ጋዜጠኞች እና የካሜራ ባለሙያዎች በምክር ቤቱ አስተባባሪዎች ከአዳራሽ እንዲወጡ ተደርገዋል። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ የስብሰባውን የመጀመሪያ ክፍል ለመዘገብ “እንዳልተፈቀደላቸው” ከተነገራቸው በኋላ፤ ለግማሽ ሰዓት ገደማ በፓርላማ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሆነው ሲጠብቁ ቆይተዋል።
ዘጋቢዎቹ የዛሬው ስብሰባ የመጀመሪያ ክፍል በዝግ መካሄዱን እና የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዕጩ የተጠቆመበት እንደነበር ያወቁት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ካደረጉት የመግቢያ ገለጻ ነው። አቶ ታገሰ በዚሁ የመግቢያ ንግግራቸው፤ የአቶ ታዬን የስራ ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት በንባብ ለሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት አቅርበዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የተወለዱት አቶ ታዬ፤ ከ1973 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተመድበው አገልግለዋል። በዲፕሎማሲው መስክ እና በመንግስት ሰራተኝነት ከአራት አስርት አመታት በላይ ልምድ ያካበቱ መሆናቸው የተገለጸው አቶ ታዬ፤ በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
አቶ ታዬ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ላንካስተር ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ስትራቴጂ ጥናት ነው። አዲሱ ፕሬዝዳንት ከዚህ በተጨማሪ በሰላም፣ አቀፍ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ላይ ሰፋ ያሉ አጫጭር ኮርሶችን እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በተለያዩ ሀገራት መወሰዳቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
በዲፕሎማሲው መስክ የካበተ ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ታዬ በዋሽንግተን፣ ሎስ አንጀለስ፣ ስዊድን እና ግብጽ በቆንስላ ጄነራልነት እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል። አምባሳደር ታዬ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ዓመታት ሰርተዋል።
በጥር ወር 2015 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ በመሆን የተሾሙት አቶ ታዬ፤ በዚህ ኃላፊነታቸው አንድ ዓመት ካገለገሉ በኋላ ባለፈው ዓመት ጥር ወር መጨረሻ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዲመሩ ተሹመዋል። አቶ ታዬ የዛሬውን ሹመት እስካገኙበት ድረስ በዚሁ የኃላፊነት ቦታቸው ላይ ቆይተዋል።
በዛሬው የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ፤ ለስድስት ዓመታት ያህል የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ስልጣናቸውን በይፋ ለአቶ ታዬ አስረክበዋል። ከዛሬው ስብሰባ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ተሰናቧቿን ፕሬዝዳንት “በኢትዮጵያ መንግስት ስም” ያመሰገኑ ሲሆን ለአቶ ታዬም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[