በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ “የጥፋት ኃይል” ሲል የጠራው ቡድን የመንግስት “ግልበጣ አውጆብኛል” ሲል ከሰሰ። በዚህ ኃይል ላይ “ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወስድ ያስታወቀው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በዚህ ሂደት ለሚፈጠር ማንኛውም አይነት ጥፋት “ብቸኛ ተጠያቂው”ይኸው ቡድን እና አመራሩ መሆኑን ገልጿል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። በትግራይ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የወጣው ይህ መግለጫ፤ የህወሓት አመራር “ለሁለት ከተሰነጠቀ በኋላ” የተከሰቱ ጉዳዮችን መለስ ብሎ ቃኝቷል።
በመግለጫው“ቡድን” በሚል የተጠቀሰው የህወሓት አመራሮች ያሉበት ስብስብ፤ የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባኤ “በህገወጥ”መንገድ ማድረጉን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውሷል። ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ የተደረገውን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ያካሄደው፤ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ጎራ ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ራሳቸውን ያገለሉበትን ይህን ጠቅላላ ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና እንደማይሰጠው ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። በዚህ ጉባኤ ላይ ዶ/ር ደብረጽዮን በድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፤ አቶ አማኑኤል አሰፋ በአቶ ጌታቸው ተይዞ የነበረውን የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ እንዲረከቡ ተደርገዋል።
የእዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች፤ 45 አባላት ያሉበት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ራሳቸውን ባገለሉት የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ምትክ ተተኪ አባላትን መምረጣቸው አይዘነጋም። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በበኩሉ ዘጠኝ አባላት ያሉበትን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዲስ መልክ መርጧል።
ከነሐሴው አወዛጋቢ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ በአቶ ጌታቸው እና በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመሩት የህወሓት ጎራዎች በየፊናቸው ህዝባዊ ስብሰባ ሲያካሄዱ እና ማስጠንቀቂያ ጭምር ያዘሉ የየራሳቸውን መግለጫዎች ሲያወጡ ቆይተዋል። በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ጎራ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ማንሳቱን አስታውቋል።
ይኸው የህወሓት ጎራ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት የካቢኔ አባላትን ጨምሮ 13 አመራሮችን በተመሳሳይ መልኩ ከኃላፊነት ማውረዱን የገለጸ ሲሆን፤ በምትካቸውም ተተኪ የፓርቲው ተወካዮችን መሾሙን ይፋ አድርጓል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ “የቡድኑ” አካሄድ የመንግስት “ግልበጣ እወጃ” እንደሆነ ገልጿል።
“የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የህዝብ አንድነትን ላለማደፍረስ በሚል የተከተለውን ትግስት እንደ ድክመት በመውሰድ፤ ይህ ቡድን ከመስከረም 27፤ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ስርዓት አልበኝነትን ለማስፈን ያለውን ፍላጎት በይፋ አውጇል። ቡድኑ መንግስትነት እንዴት እና በምን ሁኔታ እንደሚያዝ ጠፍቶት ሳይሆን፤ በትግራይ ውስጥ ሁከት እና ግርግርን ለመፍጠር እያደረገ ያለው ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው” ሲል አስተዳደሩ በመግለጫው ወንጅሏል።
ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በተቃራኒ ያለውን የህወሓት ቡድን “የስርዓት አልበኝነት”ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጀመረው፤ “የትግራይ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ወደተሻለ ደረጃ በደረበት” ወቅት መሆኑን መግለጫው አትቷል። ሆኖም ካሁን በኋላ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “ስርዓት አልበኝነትን በትግስት ማለፍ አይችልም” ሲል መግለጫው አስጠንቅቋል።
“አንድነታችን እንዳይደፈርስ በማሰብ ከዚህ በፊት በትግስት ያለፍናቸው ጊዜያት ይህ ቡድን እንደ ድክመት ወስዶ እየሰራበት መቆየቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በዚህ የጥፋት ኃይል ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጀምራል” ያለው መግለጫው፤ በዚህ ሂደት ወቅት ለሚፈጠር “ማንኛውም ጥፋት” “ብቸኛው ተጠያቂው” ይኸው ቡድኑ እና አመራሩ መሆኑን አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “የፕሪቶሪያ ውልን በሚገባ ለመፈጸም” እና “መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለማስመለስ” አቅሙን አደራጅቶ እንደሚሰራ በዛሬው መግለጫው ማጠቃለያ ላይ አመልክቷል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ህግ እና ስርዓትን ለማስከበር የጀመራቸውን ጥረቶች” በማጠናከር፤ “የትግራይ ህዝብን ስጋት የተረዳ ዘመቻ” እንደሚያደርግም ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)