⚫ ዛሬ ቤንዚን በ9 ብር ገደማ፣ ነጭ ናፍጣ በ7 ብር ገደማ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል
በሙሉጌታ በላይ
የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻን በማድረግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ በየሶስት ወሩ ጭማሪ ሊያደርግ ነው። መንግስት በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ከአንድ ዓመት በኋላ“የተሟላ ማስተካከያ” እንደሚያደርግም ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 28፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ ከዛሬ ምሽት 12 ሰአት ጀምሮ በስራ ላይ የሚውል የነዳጅ ምርቶች ችርቻሮ መሸጫ ዋጋን ይፋ ያደረገ ነው።
በዛሬው የዋጋ ማስተካከያ፤ አንድ ሊትር ቤንዚን በ9 ብር ገደማ የጨመረ ሲሆን ነጭ ናፍጣ በበኩሉ በሊትር 7 ብር ገደማ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎበታል። በዚህ መሰረት እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ በሊትር 82 ብር ከ60 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ቤንዚን፤ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በ91 ብር 14 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል።
በአዲሱ የዋጋ ማስተካከያ፤ በሊትር 83 ብር ከ74 ሳንቲም የሚሸጠው ነጭ ናፍጣ 90 ብር ከ28 ብር ገብቷል። በሊትር 70 ብር ከ83 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው የአውሮፕላን ነዳጅ፤ በአዲሱ ዋጋ በሰባት ብር ጨምሮ በ77 ብር 76 ሳንቲም ለገበያ ይቀርባል።
ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ፤ በነዳጅ ዋጋ ላይ “ከፍ ያለ ጭማሪ” ማስከተሉ ለዋጋ ጭማሪው አንደኛው መሰረታዊ ምክንያት መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የነዳጅ ምርቶች ዋጋ የፖሊሲ ማሻሻያው ይፋ ከመሆኑ በፊት በነበረበት መጠን እንዲቀጥል ለማድረግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “በሁለት ወራት ብቻ ከ35.8 ቢሊዮን ብር በላይ ለድጎማ ማውጣቱን” ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
መንግስት ይህን እርምጃ የወሰደው “የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እና በመስከረም ወር የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት በተረጋጋ ሁኔታ ለማድረግ ሲባል” መሆኑን በመግለጫው ተጠቅሷል። ሆኖም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያውን ማነሻ በማድረግ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ባለመስተካከሉ፤ እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ በስራ ላይ የነበረው መሸጫ “ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች በግማሽ ዝቅ” ያለ እንደነበርም ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
ይህ ሁኔታ መፈጠሩ፤ ነዳጅ “ለኮንትሮባንድ” እና “ለህገወጥ ንግድ” እንዲጋለጥ ማድረጉን ያመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በእነዚህ ምክንያቶች አሁን ያለውን ሀገራዊ ሁኔታዎች ባገነዘበ አግባብ “መጠነኛ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ” ማድረግ እንዳስፈለገ አትቷል። የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያው በሁሉም የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም አመልክቷል።
“በዚህም መሰረት የአለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ፤ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ በየሶስት ወሩ የሚደረግ ሲሆን መንግስት ለአንድ ዓመት የሚቆይ ጥቅል ድጎማ ያደርጋል”ሲል የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል። የድጎማው መጠን በነዳጅ አይነቶቹ መሰረት እንደሚለያይም ጠቁሟል።
መንግስት በዚህ አይነት መልኩ የሚያደርገውን ድጎማ ለአንድ ዓመት ከቀጠለ በኋላ “የተሟላ ማስተካከያ” እንደሚያደርግ ሚኒስቴሩ ገልጿል። በነዳጅ ዋጋ ላይ ለተደረገው ጭማሪ፤ ተጠቃሚው ህብረተሰብ በየሶስት ወሩ እንዲከፈል የሚጠበቀውን ዋጋ ሚኒስቴሩ በዛሬው መግለጫው የጠቀሰው “እጅግ አነስተኛ” በሚሉ ቃላት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)