በቤርሳቤህ ገብረ
በሪል ስቴት ልማት ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች “የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ”እንዲያወጡ የሚያስገድድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። አግባብ ባለው አካል፤ የሪል ስቴት ወቅታዊ ዋጋ አመላካች የሆነ “መነሻ እና መድረሻ ጣሪያ” በየጊዜው እንደሚወጣም በአዲሱ የአዋጅ ረቂቁ ተደንግጓል።
“የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ፤ በሰባት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን በውስጡ 36 አንቀጾች ይዟል። አዋጁ ከተዘጋጀባቸው ምክንያቶች አንዱ “የቤት ፈላጊዎች በእጥረት እና በገበያ ግልጽነት መጓደል ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና ለመታደግ” መሆኑ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
“የቤት እጥረት የከተሞችን አቅም እና የዜጋውን ኑሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነ መሆኑን” የሚጠቅሰው የአዋጅ ረቂቁ፤ በዚህም ምክንያት “በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ለመደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ”ድንጋጌው መዘጋጀቱን ሰነዱ ያትታል። ዛሬ ሐሙስ መስከረም 30፣ 2017 ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ፤ መንግስት ለሪል ስቴት አልሚዎች “መሬት በስፋት እንዲቀርብላቸው” የሚያደርግበትን የድጋፍ አሰራር አብራርቷል።

የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ የሪል ስቴት አልሚዎች የእዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት፤ በአዋጅ ረቂቁ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያሟሉ ነው። የሪል ስቴት አልሚዎች እንደከተሞች ደረጃ “በአንድ ጊዜ “ከ500 እስከ አምስት ሺህ የሚሆኑ ቤቶች የሚገነቡ” ከሆነ እና ከዚህ ውስጥም “40 በመቶ የሚሆነውን” ለዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍል “ተደራሽ” የሚያደርጉ ከሆነ መሬት በስፋት ሊቀርብላቸው እንደሚችል በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
የግንባታ ግብአቶችን “በፍራንኮ ቫሉታ በራሳቸው የውጪ ምንዛሬ ከውጪ ለሚያስገቡ” የሪል ስቴት አልሚዎችም፤ ከመንግስት መሬት በስፋት ለማግኘት የሚችሉበት እድል ተመቻችቶላቸዋል። ለሪል ስቴት ልማት የሚያስፈልጉት የግንባታ ግብአቶች ከውጭ እንዲገቡ የሚደረገው፤ “በጥራት እና በብዛት” በሀገር ውስጥ የማይገኙ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።
አንድ የሪል ስቴት አልሚ፤ እነዚህን ግብአቶች በመጠቀም የገነባቸውን ቤቶች በማስተላለፋ ከሚያገኘው ትርፍ “60 በመቶ የሚሆነውን”“እስከ 10 አመት ከሀገር ሳያስወጣ መልሶ የሚጠቀም ከሆነ” የእድሉ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል በአዲሱ አዋጅ ተደነግጓል። በትርፍ የሚገኘውን ገንዘብ“በሀገር ውስጥ መልሶ የመጠቀም” አካሄድ የሚተገበረው፤ ብሔራዊ ባንክ በሚፈቅደው አሰራር መሰረት እንደሆነ የአዋጅ ረቂቁ አስገንዝቧል።

ለቤት ልማት እና ግንባታ የሚጠቅሙ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርት ፋብሪካ በመገንባት፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት፣ የውጭ ምንዛሬ መቆጠብ የሚያስችል መሆኑ የተረጋገጠ የሪል ስቴት አልሚም የእዚሁ እድል ተቋዳሽ ሊሆን እንደሚችልም ለፓርላማ የቀረበው አዋጅ ያስረዳል። አዋጁ ከዚህ በተጨማሪ በከተሞች ለሪል ስቴት ልማት የሚውል ቦታ የሚቀርብበትን አግባብም ዘርዝሯል።
በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከአምስት ሺህ ቤት በላይ የሚገነባ የሚያስተላልፍ አልሚ፤ “ቅድሚያ ተሰጥቶት መሬት በስፋት ይቀርብለታል”። እንደከተሞች ተጨባጭ የቤት ፍላጎት፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶች የሚገነባ እና የሚያስተላልፍ የሪል ስቴት አልሚ በተመሳሳይ መልኩ መሬት እንደሚቀርብለት የአዋጅ ረቂቁ ይገልጻል።
ይህ አሰራር የኢንዱስትሪ ፓርክ ያለበት አካባቢ በሚገኙ ከተሞች ላይም ተግባራዊ እንደሚደረግ በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። ከዚህ ባነሰ ስፋት ቤት ለሚፈልጉ ከተሞች ደግሞ ከ500 ቤት በላይ የሚገነባ እና የሚያስተላልፍ የሪል ስቴት አልሚ፤ ቅድሚያ ተሰጥቶት መሬት እንዲቀርብለት እንደሚደረግም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል።

አዲሱ አዋጅ የሪል ስቴት አልሚዎች ለሚያሟላቸው የሚገቡ ግዴታዎችን በውስጡ አካትቷል። አንድ የሪል ስቴት አልሚ “ያለደንበኛው ፍላጎት እና ፈቃድ”፤ አጠቃላይ ግንባታው ቢያንስ 80 በመቶ ያልተጠናቀቀ ቤት “ለደንበኞች ሊያስተላልፍ አይችልም” የሚለው ከግዴታዎቹ መካከል ተጠቃሽ ነው።
የሪል ስቴት አልሚው ቤቶቹን ለመገንባት የሚያስችለውን የመሬት ይዞታ መረጋገጫ እና የግንባታ ፍቃድ ከሚመለከተው አካል ከመረከቡ በፊት፤ “ደንበኞችን መመዝገብ እና ቅድመ ክፍያዎችን መሰብሰብ” እንደማይችልም በአዋጅ ረቂቁ ላይ በግዴታነት ሰፍሯል። የሪል ስቴት አልሚው፤ ቅድሚያ መሸጥ የሚፈልገውን ቤት “የመስሪያ ቦታ”“የይዞታ ማስረጃ”፤ ቤቱ ተገንብቶ እስከሚተላለፍ ድረስ “በሚመለከተው አካል”“እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ እንዲታገድ” የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል።
አልሚው ቤቱን ሳይገነባ ለቤት ፈላጊዎች በቅድሚያ በሚሸጥበት ወቅት፤ ከቤት ገዢዎች የሚሰብሰበውን ገንዘብ አግባብ ባለው አካል ፈቃድ መሰረት “በሚከፈተው የዝግ የባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረግ እንዳለበት” የአዋጅ ረቂቁ ያስገድዳል። በዚህ መልኩ በዝግ የባንክ ሂሳብ ገቢ የተደረገው ገንዘብ የሚለቀቅበት ሁኔታ፤ ወደፊት በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰን ረቂቅ ሰነዱ ጠቁሟል።

የሪል ስቴት አልሚው ከሚመለከተው የመንግስት አካል የተሰጠውን “የይዞታ ማረጋገጫ፣ የግንባታ ፈቃድ እና የሪል ስቴት ልማት ፈቃዱን ቅጂዎች” ከውል ሰነዱ ጋር አያይዞ ለደንበኛው የመስጠት ግዴታ በአዲሱ አዋጅ ተጥሎበታል። አልሚው የገነባውን ቤት የግንባታ ዕቃዎች አይነት፣ የአርክቴክቸራል፣ ሳኒተሪ፣ ስትራክቸራል እና ኤሌክትሪካል ዲዛይንም እንደዚሁ ለደንበኛው መስጠት እንዳለበት አዋጁ ያዝዛል።
አዲሱ አዋጅ ማንኛውም በሪል ስቴት ልማት መሰማራት የሚፈልግ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ባለሃብት፤ አግባብ ካለው አካል የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበትም ያስገድዳል። የሀገር ውስጥ ባለሃብት “50 ቤቶች” አሊያም በአዋጅ ረቂቁ የተፈቀደውን “ዝቅተኛ የቤት ቁጥር” ገንብቶ ማስተላለፍ የሚችል ከሆነ፤ የሪል ስቴት አልሚ“የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ” ከሚሰጥባቸው መስፈርቶች አንዱን ያሟላል።
ለሪል ስቴት ልማት ግንባታ የሚያስፈልግ “የፋይናንስ አቅርቦት እና ምንጭ ማቅረብ የሚችል” የሀገር ውስጥ ባለሃብት የሚለው ሌላኛው መስፈርት ነው። ባለሃብቱ የቅድሚያ ቤት ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልግ ከሆነ “አግባብ ካለው አካል ፈቃድ ማቅረብ የሚችል” መሆን እንደሚጠበቅበትም በመስፈርትነት ተቀምጧል።

ለሃገር ውስጥ ባለሃብት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የተዘረዘረው ሌላኛው መስፈርት፤ “ግንባታው የሚመራበትን የፕሮጀክት ጥናት እና ዝርዝር የግንባታ መርሃ ግብር ማቅረብ የሚችል” የሚለው ነው። እነዚህን መሰረት በማድረግ ለባለሃብቱ ፈቃድ የሚሰጥ ከሆነ፤ “ለቀረበው የግንባታ ጊዜ” እንደሆነም በአዋጅ ረቂቁ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)