የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር፤ መንግስት የሎጀስቲክ ዘርፍን “ለጊዜው” ለውጭ ባለሃብቶች “ክፍት እንዳያደርግ” ጠየቀ። ማህበሩ ይህን ጥያቄ ለመንግስት ማቅረቡን ያስታወቀው፤ ትላንት ሐሙስ መስከረም 30፣ 2017 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው መግለጫ ነው።
ለጋዜጠኞች መግለጫውን የሰጡት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ውብሸት፤ ኢትዮጵያ ከሶስት አመት በኃላ የሚካሄደውን ዓለም አቀፉን የሎጀስቲክ ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧን አስታውቋል። እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው በዚሁ ጉባኤ ላይ፤ የሎጀስቲክስ ኢንዱስትሪው ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር ይደረጋል።
ማህበሩ የኢትዮጵያ የሎጀስቲክ ዘርፍን በተመለከተ ለመንግስት ጥያቄ ያቀረበው፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደነበር አቶ ዳዊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የሎጅስቲክ ዘርፍን እንዴት ማዘመን ይቻላል?” በሚል ርዕስ በተካሄደው ውይይት፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነው
የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር የሎጀስቲክ ዘርፉ “ለጊዜው ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት እንዳይደረግ” የጠየቀው፤ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ አቻዎቻቸው ጋር ለመወዳደር “የመዘጋጃ ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው” እንደሆነ አቶ ዳዊት አስረድተዋል። የውጭ ባለሀብቶች በባንክ እና በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፉ መንግስት ሲፈቅድ፤ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የመዘጋጃ ጊዜ መስጠቱን ያስታወሱት አቶ ዳዊት፤ “እኛም [ዘርፉ] ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ከመከፈቱ በፊት የጎደለንን እንድናሟላ ድጋፍ እንዲደረግልን ጥያቄ አቅርበናል” ሲሉ አብራርተዋል። (በናሆም አየለ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)