በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎችን ብዛት “በሳይንሳዊ መንገድ” የሚለይ ጥናት ሊካሄድ ነው 

በቤርሳቤህ ገብረ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎችን ብዛት “በሳይንሳዊ መንገድ” የሚሰነድ ጥናት በጋራ ሊያካሄዱ ነው። ሁለቱ ተቋማት ስራውን ለመጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በመጪዎቹ ሳምንታት ይፈራረማሉ ተብሏል።

በ1987 ዓ.ም የጸደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት፤ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ማህበረሰቦች “ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” የሚለውን ስያሜ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያስቀምጣል። ሊግባቡት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የስነ ልቦና አንድነት ያላቸው እና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር ላይ የሚኖሩ ማህበረሰቦችም እንዲሁ ከሶስቱ ስያሜዎች በአንዱ ሊጠሩ እንደሚችሉ በሕገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል። 

የፌደራሉ መንግስት አባል በሆኑ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሚወከሉት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በአሁኑ ወቅት 76 ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ቢሆንም፤ የውክልና እና የማንነት ማስከበር ጥያቄዎችን ያያዙ አቤቱታዎች በየጊዜው ለምክር ቤቱ እየቀረቡ ይገኛሉ።

ይህ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በተካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይም ተነስቶ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ፤ ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ተግዳሮት ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ “በሀገር ደረጃ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን በተገቢው መልኩ የሚገልጽ ፕሮፋይል አለመኖሩ” መሆኑን ገልጿል።

ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የማንነት መገለጫ የሆነ “አትላስ ወይም ፕሮፋይል” ጥናት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል። ይህ ጥናት እንዲካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ10 ዓመት በፊት የመግባቢያ ስምምነት ቢፈራረሙም፤ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። 

ቋሚ ኮሚቴው ለ2017 በጀት ዓመት ከያዛቸው ዋና ዋና የተግባር እቅዶች መካከል፤ ይህንኑ የመግባቢያ ሰነድ በመከለስ እና ከዩኒቨርስቲው ጋር “እንደገና በአዲስ መልክ መፈራረም” የሚለው ይገኝበታል። ሁለቱ ተቋማት ጥናቱን ለማካሄድ የሚረዳ የመግባቢያ ሰነድ፤ በቀጣይ ሳምንታት እንደሚፈራረሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሀንስ አድገህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ይህ ጥናት በኢትዮጵያ ስላሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና የቋንቋዎች ብዛት “ከግምት” ባለፈ “በትክክል በሳይንስ እና በቁጥር የተረጋገጠ መልስ መስጠት የሚያስችል” እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎች ብዛት ሲገለጽ “ከ80 በላይ እና 100 አካባቢ” እየተባለ ምላሽ እንደሚሰጥ የጠቆሙት ዶ/ር ዮሀንስ፤ የዘርፉ ተመራማሪዎች እካሁን ድረስ ቁጥራቸውን በትክክል “ወስነው መግለጽ” እንዳልቻሉ አብራርተዋል።

“አንድ ቋንቋ እና የእዚያ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ የሚባለው ያላቸው ግንኙነት ‘ተፈጥሮአዊ እና ግቡቡ ነው ወይ?’ ሚለው መታየት አለበት። አንድ ብሔረሰብ የተለያየ ቋንቋዎች ሊኖሩት ይችላል። አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ በተለያዩ ስያሜ እየተጠራ፤ ምን አልባት ቁጥርም በዝቶ ሊሆን ይችላል” ሲሉ የአካዳሚው ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የማንነት መገለጫ ፕሮፋይል ወይም አትላስ (ethnographic and linguistic atlas)ማዘጋጀት፤ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችም ሆነ ጥያቄ እያነሱ ለሚገኙ ማህበረሰቦች “በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል” የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ያቀረበው ሪፖርት አስገንዝቧል። ጥናቱ በኢትዮጵያ ለሚዘጋጁ ፓሊሲዎች “በመረጃ ምንጭነት እንዲያገለግል ያስችል ዘንድ”፤ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ስራ በትኩረት ለመስራት ቋሚ ኮሚቴው ለዘንድሮ ዓመት እቅድ ይዟል። 

ቋሚ ኮሚቴው በ2017 ሊያከናውን ካቀዳቸው ተግባራት መካከል፤ ይህንን ስራ “በቅርበት የሚመራ ተቋም በደንብ እንዲቋቋም ማድረግ” የሚለው ይገኝበታል። “የስምንት ዓመት ፕሮጀክት ፕሮፖዛል እና “የአንድ  ዓመት እቅድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ አቅርቦ ማስጸደቅ” የሚለው ሌላው በቋሚ ኮሚቴው የተግባራት ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተርም፤ አጠቃላይ ስራው በትንሹ ከአምስት እስከ ስምንት ዓመታት የሚፈጅ መሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ስራውን ይህን ያህል ጊዜ የሚወስደው፤“ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና ከስሜታዊ ውሳኔ በጸዳ መልኩ”፣ “ሳይንስ እና ቀመርን መሰረት” ተደርጎ የሚጠና በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ዶ/ር ዮሀንስ አስረድተዋል።  

በጥናቱ ሂደት ተሳታፊ የሚሆኑት ባለሙያዎችም “በምርምር ስራዎቻቸው የተመሰከረላቸው” እንደሚሆኑ የአካዳሚው ዳይሬክተር አመልክተዋል። የአትላሱ መዘጋጀት ከጥናት እና ከምርምር ፍጆታ በዘለለ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ላሉ “ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች፣ ኢኮኖሚያዊ መወለጋገዶች እና አስተዳደራዊ እንከኖች” “መፍትሄ ሰጪ” እንደሚሆን ዶ/ር ዮሀንስ ተስፋቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)