በሙሉጌታ በላይ
መንግስታዊ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው ኢትዮ ቴሌኮም፤ “ለመጀመሪያ ዙር” እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸውን 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ለሽያጭ አቀረበ። ተቋሙ ይህንን የገለጸው 10 በመቶ የባለቤትነት ድርሻውን በይፋ ለህዝብ መሸጥ መጀመሩን ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 6፤ 2017 ባስታወቀበት መርሃ ግብር ላይ ነው።
በካፒታል ገበያ በኩል ለሽያጭ የቀረበውን የኢትዮ ቴሌኮምን አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ፤ እስከ 3,333 አክስዮን ድረስ መግዛት እንደሚችል ተገልጿል። ይህ ከፍተኛ የአክሲዮን መጠን ለገበያ የቀረበው፤ 1.5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እና ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር በ999,000 ብር ነው።
አንድ “ግለሰብ ወይም ባለሀብት” የኢትዮ ቴሌኮምን ዝቅተኛ አክሲዮኖችን ለመግዛት 9,900 ብር ያስፈልገዋል። ይህ የገንዘብ መጠን ለ33 አክሲዮኖችን የቀረበ ሲሆን፣ የአገልግሎት ክፍያ እና ተጨማሪ እሴት ታክስን አያካትትም።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 25፤2017 በሚቆየው የአክሲዮን ሽያጭ የሚከናወነው፤ “ቴሌብር” በተሰኘው የኢትዮ ቴሌኮም ሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መተግበሪያ መሆኑን ተቋሙ ጨምሮ አስታውቋል። በአክሲዮን ግዢው ላይ የሚሳተፉ ዜጎች የገንዘብ ክፍያውን “በሁለት ቀናት ውስጥ” ከፍለው ማጠናቀቅ እንዳለባቸውም አመልክቷል።
በግብይቱ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን “ማንነታቸውን የሚገልጽ ህጋዊ ሰነድ”ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም፤ የግዢውን ማመልከቻ በሌላ ሰው የሚፈጽሙ ከሆነ በተመሳሳይ መልኩ ተወካዮቹ “ህጋዊ የውክልና ማረጋገጫ ሰነድ” እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሟል።
በዚህ መልክ የተገዙ መደበኛ አክሲዮኖችን “የመሸጥ፣ የመተላለፍ እና ከማንኛውም መደበኛ አክሲዮን ወደ ሌላ ባለቤትነት ማስተላለፍ” የሚቻለው፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ (ካፒታል ገበያ) የመካተቱ ሂደት ሲጠናቀቅ መሆኑን አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ስለ አክሲዮኖች ዋጋ የተጠቀሰው ማስተካከያ ተደርጎበታል]