በቤርሳቤህ ገብረ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችን እና በጸጥታ መደፍረስ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማቋቋም፤ በዚህ ዓመት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። ክልሉ ለመልሶ ማቋቋም ስራው የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን የሚያፈላልግ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ከትላንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 3፤ 2017 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ኮሚቴው “በአጭር ጊዜ ወደ ስራ እንዲገባ” ውሳኔ አስተላልፏል። የገቢዎች፣ የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎችን በውስጡ ያካተተው ኮሚቴው፤ የክልሉ ማህበረሰብ እና የተለያዩ ድርጅቶችን አስተባብሮ የሚፈለገውን የገንዘብ መጠን የማሰባሰብ ስራን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑም ተነግሯል።
የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴውን ማደራጀት ያስፈለገው፤ የክልሉ መንግስት ካለው የበጀት ውስንነት አንጻር ስራውን በራሱ አቅም ብቻ ለማከናወን የማይቻል በመሆኑ ምክንያት መሆኑን የክልሉ የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሻሪፍ ሃጂ አኑር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ክልሉ ለመልሶ ማቋቋም በዚህ ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደው ከ130 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አሻሪፍ፤ ሆኖም ለአጠቃላይ ስራው ከዚህም በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ2017 በጀት ዓመት እቅድ ማስፈጸሚያ የያዘው በጀት 8.9 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ በጀት ውስጥ 3.7 ቢሊዮን ብሩ፤ የፌደራል መንግስት ለክልሉ በድጎማ የሚሰጠው ነው። ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ከሚጠጋው ከዘንድሮው የክልሉ በጀት ውስጥ፤ ምን ያህሉ ለመልሶ ማቋቋም ስራ እንደሚውል ከ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አሻሪፍ፤ ዝርዝሩን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የመልሶ ማቋቋም ስራው፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጣቂዎች እና ተፈናቃዮች “ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ” የማድረግ አላማ ያነገበ መሆኑን የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊው አመልክተዋል። ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱት የቀድሞ ታጣቂዎች፤ “በእርሻም፣ በማእድንም ይሁን በመረጡት እና ያዋጣናል በሚሉት ዘርፍ” እንዲሰማሩ እንደሚደረግ አቶ አሻሪፍ አብራርተዋል።
“መንግስት ጥናት ያደርጋል። ያንን ጥናት ይቀርብላቸዋል። የተለያዩ የስራ ዘርፎች አሉ። በዚያ በሚመርጡት የስራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ፤ መንግስት ማድረግ ያለበትን እገዛ ያደርጋል” ሲሉ የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለቀድሞ ታጣቂዎች እገዛ ሲያደርግ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) እና የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን)፤ ከክልሉ መንግስት ጋር “በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን” የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ፤ በሰላም ለተመለሱ የቀድሞ ተዋጊዎች ተመሳሳይ እገዛ ተደርጓል።
ከስምምነቱ በኋላ ለእነዚህ ታጣቂዎች የክልሉ መንግስት ከ300 ሚሊየን ብር በላይ መድቦ፤ በእርሻ ለሚሰማሩት ትራክተሮች፣ በማዕድን ዘርፍ ለተደራጁት ደግሞ የወርቅ ማሽን ገዝቶ ማከፋፈሉን የቤህነን ሊቀመንበር አቶ አብዱሰላም ሸንገል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በአገልግሎት እና በንግድ ዘርፍ ለተደራጁ የቀድሞ ተዋጊዎችም፤ ለመንቀሳቀሻ የሚሆናቸው “ካፒታል” እንደተሰጣቸው አቶ አብዱሰላም አክለዋል።
በ2016 በጀት አመት ይህንን ድጋፍ ያገኙት፤ በ612 ማህበራት የተደራጁ እና 9,734 የቀድሞ ታጣቂዎች መሆናቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጭምር የሆኑት አቶ አብዱሰላም አመልክተዋል። ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ ቀሪ ታጣቂዎችን ለማደራጀት፤ ባለፈው ዓመት የተመደበውን ያህል በጀት እንደሚያስፈልግም ኃላፊው ግምታቸውን አስቀምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)