በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ በ13 ሰዓት ልዩነት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ። ዛሬ ሐሙስ እኩለ ቀን ገደማ የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል ሲለካ 4.7 የተመዘገበበት እንደሆነ የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል ገልጿል።
ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 7፤ 2017 የተከሰተው ከመተሐራ ከተማ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 34 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ የደረሰ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን በሚመዝግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል። የመሬት መንቀጥቀጡ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ንዝረት ማስከተሉን ነዋሪዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሲገልጹ ተስተውለዋል።
በትላንትናው ዕለት ምሽት እኩለ ለሊት አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚሁ አካባቢ ተከስቶ እንደነበር የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት መረጃ አመልክቶ ነበር። ርዕደ መሬቱ የደረሰበት ቦታ ከአዋሽ በስተሰሜን 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑም በመረጃው ተጠቅሷል።
የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ብቻ በአዋሽ አካባቢ የተከሰቱ ተመሳሳይ ክስተቶችን ስምንት አድርሶታል። ባለፈው እሁድ በዚሁ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ሲሆን፤ ከሳምንት በፊት ደግሞ መጠኑ በሬክተር ስኬል 4.9 የደረሰ ርዕደ መሬት በተመሳሳይ አካባቢ አጋጥሟል።
ከ2.5 እስከ 5.4 የሚደርሱ እና በሬክተር ስኬል የመለኪያ መሳሪያ የሚመዘገቡ የመሬት መንቀጥቀጦች ንዝረታቸው ሊሰማ የሚችል ነገር ግን አነስተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ከአሜሪካው ሚቺጋን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል። በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት የሚያስከትሉ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 የሚመዘገቡ መሆናቸውን የዩኒቨርስቲው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)