በአዋሽ አካባቢ በ11 ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 6 ፤ 2017 ምሽት በአዋሽ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። የመሬት መንቀጥቀጡ ያስከተለው ንዝረት፤ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች መሰማቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከአዋሽ ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ላይ የተመዘገበ እንደነበር መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል። በዚሁ አካባቢ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ብቻ ሰባት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን መረጃዎች ያሳያሉ። 

ባለፈው እሁድ በተመሳሳይ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ ነበር። ከዚህ ክስተት አንድ ሳምንት አስቀድሞ መስከረም 26፤ 2017 ምሽት በዚያው ስፍራ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 የደረሰ ነበር።

መስከረም 16፤ 2017 ለአርብ አጥቢያ ከሌሊቱ 6:36 አካባቢ በአዋሽ፣ ፈንታሌ እና ዶፈን አካባቢ ተመሳሳይ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተመዝግቧል። በዚሁ ዕለት ከሁለት ሰዓታት ቆይታ በኋላ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.5 ገደማ የተመዘገበ እንደነበር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ባለሙያዎች በወቅቱ መግለጻቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)