የኮሪደር ልማቱ “የሚቋረጥ ነገር መስሎት የሚያስብ ሰው ካለ፤ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል”- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስታቸው የጀመረውን የከተማ ኮሪደር ልማት “ሳያቋርጥ” እንደሚቀጥል ገለጹ። የኮሪደር ልማቱ “የሚቋረጥ ነገር መስሎት የሚያስብ ሰው ካለ፤ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል” ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም፤ 10 በመቶ የሚሆነውን አክሲዮኑን ለሽያጭ ማቅረቡን ይፋ ባደረገበት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። አብይ በዚሁ ንግግራቸው፤ “በአፍሪካ በስንዴ፣ በቡና እና በአንዳንድ ምርቶች የተሻለ ውጤት ማምጣት”መቻሉን አመልክተዋል። 

በእርሳቸው አነሳሽነት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት “የተሻለ ውጤት ማሳየት ችለናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኮሪደር ልማትን በተመለከተ “በጣም ብዙ ውዥንብሮች እንዳሉ አውቃለሁ” ያሉት አብይ፤ አዲስ አበባን በተመለከተ የተከናወኑ ስራዎች በሙሉ “ሰው ተኮር” መሆናቸውን አስገንዘበዋል።

“ሰው እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ስራችን ግን አይቋረጥም። ገና እናፈርሳለን፤ ገና እንገነባለን። የሚቋረጥ ነገር መስሎት የሚያስብ ሰው ካለ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።  “አዲስ አበባ አፍሪካ ላይ ካሉ ከተሞች ገና ነች። አሁንም፤ እንኳን ከአለም ከአፍሪካ ገና ነች። ገና ሲጀመር የሚቆም ስራ መኖር የለበትም” ሲሉም አክለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ማሳሰቢያ፤ ከሁለት ቀናት በፊት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ካወጣው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)አቋም ጋር የተቃረነ ሆኗል። የኢህአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰኞ ጥቅምት 4፤ 2017 በሰጠው መግለጫ፤ በመዲናዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት “የህዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮችን” ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቅቆ ነበር። 

የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን “ሰብአዊ መብቶች የጣሰ ነው”ያለው ኢህአፓ፤ በዚሁ ሳቢያ የህዝብ “ብሶት እና ምሬት” እያየለ መምጣቱን ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለነዋሪዎች ምሬት“ትኩረት እና ቅድሚያ” በመስጠት አስፈላጊውን “የእርምት እርምጃ” በአፋጣኝ እንዲወስዱም ፓርቲው አሳስቧል። 

በዚሁ ዕለት ኢህአፓን ጨምሮ አራት ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በአዲስ አበባ “የወንዝ ዳር ልማት”፣ “የጫካ ፕሮጀክት” እና “የኮሪደር ልማት” በሚል እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ምክንያት “የመቶ ሺህዎች ህይወት እየተመሰቃቀለ” እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ከኢህአፓ ጋር መግለጫውን ያወጡት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ፤ የኮሪደር ልማቱን “ኢ-ህገ መንግስታዊ፣ አግላይ፣ የበላይ እና የበታች አካሄድ” የሰፈነበት ነው በሚል ተቃውመውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)