በትግራይ ክልል ከጦርነት አስቀድሞ ለተሰጡ ብድሮች “ፖለቲካዊ መፍትሔ” እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ እየተካሄደ ነው

በቤርሳቤህ ገብረ

በትግራይ ክልል ከተካሄደው ጦርነት በፊት ለንግዱ ማህበረሰብ ተሰጥተው መመለስ ያልቻሉ ብድሮች እና ወለድን በተመለከተ፤ የፌደራል መንግስት “ፖለቲካዊ መፍትሔ” እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ በክልሉ ባሉ 52 ከተሞች እየተካሄደ ነው። አርብ የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ በነገው ዕለት ተጠናቅቆ “ወደ ክልሉ ማዕከል ይላካል” ተብሎ እንደሚጠበቅ የትግራይ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በትግራይ ከተቀሰቀሰው ጦርነት አስቀድሞ፤ በክልሉ የፋይናንስ ተቋማት ተሰጥቶ የነበረው ብድር 31 ቢሊየን ብር እንደነበር ምክር ቤቱ አመልክቷል። ይህ ብድር ወለዱን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 70 ቢሊዮን ብር ገደማ መድረሱን ምክር ቤቱ አመልክቷል።   

በትግራይ ክልል ከተሞች በሚገኙ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የፊርማ ማሰባሰብ፤ የፌደራል መንግስት ወለዱን እንዲሰርዝ አና ለተሰጡት ብድሮች ጦርነቱ እንዳስከተለው ጉዳት መጠን “ተመጣጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ” የሚጠይቅ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በፊት ተሰጥተው ለነበሩ ብድሮች፤ ባንኮች እስከ ታህሳስ 2017 ዓ.ም. የመክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙላቸው በሰኔ 2015 ዓ.ም. በሰርኩላር ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

ብሔራዊ ባንክ የሰጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ሁለት ወር በቀረበት ወቅት፤ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ “ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት ያለመ” መድረክ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በመቐለ ከተማ ተካሄዷል።  የትግራይ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት እንዲሁም የክልሉ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች በጋራ በካሄዱት በዚህ ስብሰባ ላይ፤ በየከተሞቹ ከሚገኙ ነጋዴዎች የፊርማ ማሰባሰብ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

በዚህ ውሳኔ መሰረትም በ51 የትግራይ ክልል ከተሞች የሚገኙ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች፤ ባለፈው ሳምንት አርብ እና ቅዳሜ ነጋዴዎችን ሰብስበው ውይይት አድርገዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በአክሱም፣ አድዋ እና አዲግራት ከተሞች የሚገኙ የማህበራት ምክር ቤቶች ኃላፊዎች፤ ፊርማ የማሰባሰብ መርሃ ግብሩን የዚያኑ ዕለት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መልኩ እየተሰበሰበ የሚገኘው የነጋዴዎች ፊርማ፤ ለፌደራል መንግስት ጥያቄ እንዲያቀርብ በትግራይ ክልል  ደረጃ ለተቋቋመው ግብረ ኃይል እንደሚሰጥ የትግራይ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ በሪሁን ሀፍቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ግብረ ኃይሉ የተሰበሰቡትን ፊርማዎች፤ የነጋዴ ማህበረሰብ ድጋፍ እና መግባባት የተደረሰበት መሆኑን በማስረጃ ሰነድነት እንደሚያቀርበውም አክለዋል። 

ብድር እና ወለድን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለፌደራል መንግስት እንዲያቀርብ ከሁለት ሳምንት በፊት የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስራ ሰባት አባላት ያሉት ነው። በግብረ ኃይሉ ውስጥ የትግራይ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት እንዲሁም የትግራይ ክልል ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንቶች እና የቦርድ አባላቶቻቸው ተካትተዋል። በክልሉ ያሉ ታዋቂ ባለሃብቶች  እና ምሁራኖችም የግብረ ኃይሉ አባል ተደርገዋል። 

ባለፈው አርብ በአዲግራት ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ላይ፤ ግብረ ኃይሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ በመሄድ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ሃሳብ መቅረቡን የከተማው የንግድ እና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዲበኩሉ አለም ብርሃነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለነጋዴዎች ብድር ያቀረቡ ባንኮችም የራሳቸውን መፍትሔ እንዲያፈላልጉ በስብሰባው ተሳታፊዎች ጥያቄ መቅረቡንም አስረድተዋል።

በብድር ረገድ ያለው ችግር ካልተፈታ፤ የንግድ ማህበረሰቡ “ከባንኮቹ ጋር ያለው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ” እስከመወሰን የደረሰ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በስብሰባው ተሳታፊዎች መወሰኑንም አቶ ዲበኩሉ  አብራርተዋል። ለችግሩ እልባት ካልተበጀለት፤ ጉዳዩ “እስከ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት” ድረስ ተወስዶ እንዲታይ “ሰላማዊ ትግል” መደረግ እንዳለበትም የስብሰባው ተሳታፊዎች ማሳሰባቸውንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)