የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እገዳ ጣለ 

ሶስት ፓርቲዎች እግዱን በመቃወም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብተዋል

በሙሉጌታ በላይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ 11 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማናቸውንም ህጋዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አገደ። ቦርዱ ያስተላለፈው የእግድ ውሳኔ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሚያዘጋጃቸው ጉባኤዎች ላይ እንዳይገኙ እና በምክር ቤቱ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉም ይከለክላል።

ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላይ እገዳ የጣለው፤ ትላንት ሰኞ ጥቅምት 11፤ 2017 ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው። ቦርዱ ለእገዳው በምክንያትነት የጠቀሰው “በጠቅላላ ጉባኤ”፣ “በኦዲት” እና “በሴት አባላት” ብዛት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ምክንያት ፓርቲዎቹ ፈጽመዋቸዋል ያላቸውን ጥሰቶች ነው። 

ቦርዱ የእግድ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት፣ የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ፣ የገዳ ስርአት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ እና የአገው ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገኙበታል። እገዳ ከተጣለባቸው ፓርቲዎቹ አንዱ የሆነው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ፍሰሃ፤ በፓርቲያቸው ላይ ውሳኔው የተላለፈው “የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች አባላትን መረጃ አላቀረበም” በሚል ምክንያት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ይህን መረጃ እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ ደብዳቤ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ሆኖም ፓርቲያቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የአባላቱን መረጃ ለመሰብሰብ “በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዳልፈቀደለት” አስረድተዋል። ፓርቲው ይህንኑ ችግሩን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁንም አመልክተዋል።

“ፓርቲው ሀገር አቀፍ ፓርቲ ነው። ሰዎች ተንቀሳቅሰው፤ አባሎቻችን ጋር ሄደው መረጃ አሰባስበው ነው ይዘው የሚመጡት። ‘አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ አይፈቅድልንም፤ የሁለት ዓመት ጊዜ ይሰጠን። ሀገሪቷ ከተረጋጋች በኋላ እናመጣለን። የቦርዱን ትእዛዝ እና መመሪያ እንቀበላለን’ብለናቸዋል”ሲሉም አዲስ ትውልድ ፓርቲ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ማብራሪያ አስታውሰዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ቦርድ የእገዳ ውሳኔ ማስተላለፉ፤“በሰላማዊ ትግል የሚታገሉ ፓርቲዎችን ከሰላማዊ ትግል ለማውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው” ሲሉ አቶ ሰለሞን ተችተዋል። የገዳ ስርአት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሮበሌ ታደሰም የምርጫ ቦርድ ውሳኔ “የሰላም ትግሉ ላይ በር መዝጋት ነው” በማለት የተቃውሞ አስተያየታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሰጥተዋል።

ፓርቲያቸው ግንቦት 20፤ 2015 ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጉን የሚገልጹት አቶ ሮበሌ፤ “ለፓርቲው 12 አመራር ለመምረጥ 30 እጩ ማቅረባችሁ ተገቢ አይደለም” በሚል ምክንያት ፓርቲው በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉን አስረድተዋል። አቶ ሮበሌ ይህንን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ“ትክክል ያልሆነ”ሲሉ ነቅፈውታል። 

አቶ ሮበሌ የሚመሩት የገዳ ስርአት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ እና የአገው ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 12፤ 2017 ዓ.ም የምርጫ ቦርድን የእግድ ውሳኔ በመቃወም  ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልጸዋል። ሶስቱ ፓርቲዎች ለምክር ቤቱ ያስገቡት ደብዳቤ፤ የእግድ ደብዳቤው መስከረም 26፤ 2017 እንደደረሳቸው ይገልጻል። 

ምርጫ ቦርድ “ወቅቱን ባልጠበቀ እና ጊዜን በማይዋጅ ሁኔታ ደብዳቤዎችን እየጸፈ በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ላይ ችግር እየፈጠረብን ድርጅታዊ ስራዎችን ለመስራት ተቸግረናል” ሲሉም ፓርቲዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት “መድረክ በመፍጠር” ከቦርዱ ጋር “መፍትሔ እንዲያፈላልግ” ፓርቲዎቹ በደብዳቤው ጠይቀዋል።

የሶስቱ ፓርቲዎች ደብዳቤ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መድረሱን፤ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የጋራ ምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ከሶስቱ ፓርቲዎች የቀረበለትን አቤቱታ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍም ሰብሳቢው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)