ከመደበኛ እስር ቤቶች ውጭ የሚታሰሩ ሰዎች ሁኔታ “አሳሳቢ” ሆኖ መቀጠሉን ኢሰመኮ ገለጸ

በናሆም አየለ

ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ “በተራዘመ እስር”፣ “መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች”፣ እንዲሁም “በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ“ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታ፤ “አሳሳቢ” ሆኖ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ። የድርጊቱ ተጎጂዎች፤ ሲቪል እና የደንብ ልብስ በለበሱ የታጠቁ የጸጥታ አካላት “የህግ ስነ ስርዓት ባልተከተለ ሁኔታ” “በግዳጅ እንደሚያዙም” ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው፤ “የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን” በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 13፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው፤ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከ52 በላይ የሆኑ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ መቆየታቸውን ይፋ አድርጓል።  

የዛሬው መግለጫ እስከወጣበት ቀን ድረስ፤ 44 ሰዎች በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከአንድ ወር እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ መለቀቃቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል። በእነዚህ ቦታዎች እንዲቆዩ ከተደረጉ ግለሰቦች መካከል “ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የነበሩ ግለሰቦች” ጭምር እንደሚገኙበት ባደረገው ምርመራ ማረጋገጥ መቻሉን ኮሚሽኑ ገልጿል። 

ሆኖም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሚያስተዳድራቸው ተቋማት ስር ባሉ “መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ቦታዎች “ተይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ሁኔታ ለማጣራት አለመቻሉን ኢሰመኮ አመልክቷል። ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ “በተራዘመ እስር”፣ “መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች”፣ “በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ ውስጥ” የሚገኙ ሰዎች ሁኔታ “አሳሳቢ” ሆኖ መቀጠሉንም ኮሚሽኑ በመግለጫው በአጽንኦት አንስቷል።   

ከመደበኛ እስር ቤቶች ዉጭ ባሉ ማቆያ ቦታዎች ላይ በሚታሰሩ ሰዎች ላይ “ድብደባ እና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው”የገለጸው ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤ እስረኞቹ “መሰረታዊ የመጸዳጃ፣ የመኝታ፣ የንጽህና መጠበቂያ አቅርቦቶች እንዲሁም በቂ ምግብና የመጠጥ አቅርቦት” በተጓደለበት ቦታእንዲቆዩ እንደሚደረጉም አብራርቷል። 

“ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተገቢውን የሕግ ስነ ስርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን እና በእስር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውሃ የማይቀርብላቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ለየብቻቸው ተለይተው ተይዘው የቆዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ” ሲል የዛሬው የኮሚሽኑ መግለጫ አትቷል።

“ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተገቢውን የሕግ ስነ ስርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን እና በእስር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውሃ የማይቀርብላቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ለየብቻቸው ተለይተው ተይዘው የቆዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ”

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

በዚህ አይነት ሁኔታ ተይዘው የቆዩ ግለሰቦች ከእስር ሲለቀቁ፤ “አይናቸው ተሸፍኖ በተሽከርካሪ ከተጫኑ በኋላ በምሽት በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች እንዲወርዱ እንደሚደረጉ” ኢሰመኮ ተጎጂዎችን እማኝ አድርጎ አስታውቋል። ከተጎጂዎች መካከል “ለመጓጓዣ” በሚል ከ300 እስከ አንድ ሺህ ብር ተሰጥቷቸው የተለቀቁ እንዳሉ ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል። 

ሁሉም ተጎጂዎች በእራሳቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ “ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት”እንዲሁም “ከፍተኛ የስነ ልቦና ቀውስ መድረሱን፤ አሁንም የሚኖሩት “በስጋት” ውስጥ እንደሆነ እንደሚያስረዱ በመግለጫው ሰፍሯል። ከእስር ከተለቀቁ ግለሰቦች ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ብር የከፈሉ መኖራቸው፤ “የጉዳዩን አሳሳቢነት እና አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን በተጨማሪ የሚያጠናክር ነው” ብሏል ኮሚሽኑ። 

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ “ያሉበት ቦታ ሳይታወቅም በተራዘመ እስር፣ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች፣ እንዲሁም በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ” ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ላይ “የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደሚደርስባቸው”አጽንኦት ሰጥተዋል። ለእነዚህ ተጎጂዎች እና አሁንም ያሉበት ሁኔታ የማይታወቁ ሰዎችን ጉዳይ በተመለከተ፤ የመንግስት የጸጥታ አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡም ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል። 

“አሰራራቸው፣ አስተዳደራቸውና አድራሻቸው ግልጽ ባልሆኑ” መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ላይ የታሰሩ ሰዎች “ለከፍተኛ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚዳርጉበት ዕድል ሰፊ” መሆኑንም ራኬብ ጠቁመዋል። በዚህ አይነቱ አያያዝ “ተገቢውን ምርመራ ለማድረግ እና ተጠያቂነትን ለማስገኘት” አዳጋች መሆኑን የገለጹት ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነሯ፤  አሰራሩ “ሊቆም እንደሚገባ” አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)