በሙሉጌታ በላይ
“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 13፤ 2017 በአዲስ አበባው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ለጋዜጠኞች ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ “በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ተከልክሏል” በመባሉ ሳይከናወን ቀረ። ፓርቲው መግለጫውን የጠራው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ቅድመ እውቅና ማግኘቱን ተመልክቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ለማሳወቅ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ)የቀድሞ አመራር የነበሩት አቶ ሀብታሙ ኪታባን ጨምሮ ዘጠኝ አደራጅ ኮሚቴ አባላት ያሉት አዲሱ ፓርቲ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ እውቅና ፈቃድ ያገኘው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። የመስራች ጉባኤውን ለማድረግ የድርጅት ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኘው ፓርቲው፤ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ያላቸውን እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ለጋዜጠኞች ጥሪ ያደረገው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው።
ይህንኑ መግለጫ ለመዘገብ ዛሬ ረፋዱን 10 ጋዜጠኞች በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ቢገኙም፤ መርሃ ግብሩ ከተያዘለት ጊዜ በግማሽ ሰዓት ያህል በመዘግየቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ለአደራጅ ኮሚቴ አባላቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል። የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባላት፤ ለጋዜጠኞቹ “ትንሽ ጠብቁን። ለሁላችሁም በጋራ መረጃ እንሰጣችኋለን” የሚል ምላሽ ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ፤ የዛሬው መግለጫ “መከልከሉን” አሳውቀዋል።

የኮሚቴው አባላት መግለጫ እንዳይሰጡ መከልከላቸውን ለጋዜጠኞቹ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ ኪታባ፤ ፓርቲው ጉዳዩን አስመልክቶ ወደፊት ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባል ግን የዛሬው ክልከላ የተደረገው በመንግስት “የደህንነት አባላት” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“[የሆቴሉን]አዳራሽ ቡክ አድርገን ተከራይተን፤ ክፍያም ፈጽመን ነበር። በኋላ ግን በሰአቱ መግለጫውን ለመስጠት ወደ አዳራሽ ስንገባ፤ የሆቴሉ ኃላፊዎች የደህንነት ሰዎች መሰብሰብ እንደማንችል እንደከለከሏቸው እና ሊያስተናግዱን እንደማይችሉ ነው የገለጹልን” ሲሉ እኚሁ የኮሚቴ አባል አስረድተዋል።
ፓርቲው በዛሬው ዕለት ያጋጠመውን ክስተት ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን የአደራጅ ኮሚቴው አባል አክለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለ ክስተቱ አቤቱታ ቀርቦለት ለማረጋገር ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም። የዛሬውን መግለጫ ለማስተናገድ ተዋውሎ እንደነበር የተገለጸው የዋቢ ሸበሌ ሆቴል አንድ የስራ ኃላፊ፤ የክልከላውን ምክንያት እርሳቸው መናገር እንደማይችሉ እና ከፓርቲው የኮሚቴ አባላት ማግኘት እንደሚቻል በስፍራው ለነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ አስረድተዋል።

“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ፓርቲ፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ፣ ለአንድነት ተሰባስበን ተደራጅትን እንታገላለን፤ ለውጥ እናመጣለን” በሚሉ አደራጆች የተመሰረተ ነው። ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ ቅድመ እውቅና ካገኘበት ወዲህ ባሉት ሁለት ወራት ጊዜያት ውስጥ፤ “በሁሉም ክልሎች” የአባላት ፊርማ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በ2011 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፤ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት አስር ሺህ መስራች አባላት ሊኖሩ ይገባል። ከእነዚህ መስራች አባላት ውስጥ 40 በመቶው የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪ መሆን እንዳለባቸው አዋጁ ይደነጋጋል። ቀሪዎቹ አባላት ቢያንስ በሌሎች አራት ክልሎች ውስጥ መደበኛ ነዋሪ መሆን እንዳለባቸውን በአዋጁ ሰፍሯል።
ጊዜያዊ ፈቃድ የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ፤ በምርጫ ቦርድ ዋና ምዝገባ ለማካሄድ፤ መስራቾች የፈረሙበት እና ለሕዝብ በይፋ የሚገለጽ ሰነድ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት በዚሁ አዋጅ ላይ ተቀምጧል። የፖለቲካ ፓርቲው መመስረቻ ጽሑፍ፣ ፕሮግራም እና የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስም፣ አድራሻ እና ፊርማም እንዲሁ ከማመልከቻቸው ጋር ተያይዞ ለምርጫ ቦርድ መቅረብ ይኖርበታል።

“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” ፓርቲ ፕሮግራም፣ ፖሊሲዎች እና ሌሎች ሰነዶች በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ተናግረዋል። እነዚህ ሰነዶች ከሶስት ወራት በኋላ በሚደረገው የፓርቲው መስራች ጉባኤ ላይ እንደሚጸድቁ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፤ ለፓርቲዎች የሚሰጠው ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የሚያገለግለው ለሶስት ወራት ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሆኖም አመልካች ፓርቲዎች በቂ ምክንያት ያቀረቡ እንደሆነ፤ ጊዜያዊ ፈቃዱ ለተጨማሪ ሶስት ወራት ሊራዘም እንደሚችል በዚሁ አዋጅ ላይ ተመልክቷል።
ከፓርቲው ከአደራጅ ኮሚቴ አባል ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ፓርቲው “በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ የምስረታ ጉባኤውን እንደሚያደርግ” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሆኖም የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም እና የአመራሮቹን ማንነት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)