ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች፤ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተነገረ  

በቤርሳቤህ ገብረ

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ የሶስት ወራት አፈጻጸም፤ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ83 በመቶ በመጨመሩ፤ 1.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። በአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ጭማሪ ቢታይም፤ ወደ ውጭ ከተላኩ የጫት እና የጥራጥሬ ምርቶች የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ይህ የተገለጸው፤ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገር ከሚልኩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 14፤ 2017 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው። በዚሁ ስብሰባ ላይ የዘንድሮ በጀት ዓመት የሶስት ወራት የወጪ ንግድ እቅድ አፈጻጸም ለተሰብሳቢዎች ቀርቧል። በአዲሱ የጥራጣሬ እና የቅባት እህሎች የቀጥታ ግዢ መመሪያ ላይም ውይይት ተደርጓል።

በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ በረከት መሰረት፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ ሊገኝ ታቅዶ የነበረው አጠቃላይ ገቢ 1.12 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል። በሩብ ዓመቱ ሀገሪቱ ከዘርፉ ያገኘችው ገቢ በእቅድ ከታየዘው በ385 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብልጫ ያለው እንደሆነም አመልክተዋል።

በትላንቱ ስብሰባ ላይ የግብርና፣ የማዕድን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ክትትል ከሚያደርጉባቸው የወጪ ምርቶች እንዲሁም ከኤሌክትሪክ እና ሌሎች አገልግሎቶች የተገኙ ገቢዎች በዝርዝር ቀርቧል። በወጪ ንግድ ከፍተኛ የሆነው ገቢ የተገኘው፤ በግብርና ሚኒስቴር ክትትል ከሚደረግባቸው እንደ ቡና እና አበባ ካሉ ምርቶች ነው።

ከእነዚህ ምርቶች ባለፉት ሶስት ወራት የተገኘው ገቢ 638 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አቶ በረከት ለስብሰባው ተሳታፊዎች አስታውቀዋል። በገቢ ደረጃ ሁለተኛው ከፍተኛ መጠን የተመዘገበው በማዕድን ዘርፍ ነው። በሩብ ዓመቱ ከዘርፉ ከተገኘው 567 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የያዘው የወርቅ ምርት መሆኑ ተገልጿል። 

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከችው የወርቅ ምርት ያገኘችው ገቢ፤ 561 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አቶ በረከት ተናግረዋል። የዘርፍ ስራ አስፈጻሚው የወርቅ ምርትን የሩብ ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸም የገለጹት “ትልቅ ተአምር” በሚሉ ቃላት ነበር።

የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ከአምና በፊት በነበሩት ሁለት ዓመታት “በከፍተኛ መጠን መቀነሱ” በፓርላማ ጭምር መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። ሀገሪቱ በ2015 በጀት ዓመት ሶስት ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ ያቀረበችው የወርቅ መጠን ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር “ዝቅተኛ” ነበር። በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወርቅ ሽያጭ የተገኘው ገቢም “አጥጋቢ” አለመሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር በወቅቱ ገልጿል።

በዚህ ጊዜ ከወርቅ የተገኘው ገቢ 58 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል። በዘንድሮ በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የተገኘው ገቢ ከአምናው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር፤ የ540 ፐርሰንት እድገት የተመዘገበበት እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዢው አቶ ማሞ ምህረቱ ባለፈው መስከረም ወር በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር።   

“አምና ከወርቅ በአመቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ወደ 255 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። አምና አመቱን ሙሉ ያገኘነውን የወርቅ ገቢ፤ ዘንድሮ የእርሱን እጥፍ በሶስት ወር ማግኘት ችለናል። ይሄ ሌላው የውጭ ምንዛሬ ሪፎርምን ስኬት የሚያሳይ ነው” ሲሉ አቶ ማሞ በገቢ ረገድ የተመዘገበውን ከፍተኛ ልዩነት ዋነኛ ምክንያት አብራርተው ነበር።

የውጭ ምንዛሬ ተመን “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት” መሸጋገሩ ይፋ የተደረገው በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ነበር። የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ “በገበያ ላይ የተመሰረተ” መሆኑን ተከትሎ፤ “ወደ ጎረቤት ሀገሮች ይሄድ የነበረው የወርቅ ምርት፤ ወደ ኢኮኖሚው እንዲመጣ ሆኗል” ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዢው በማብራሪያቸው አመልክተዋል።

አዲሱ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት እንደ ወርቅ ምርት ሁሉ፤ በቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ላይ በጎ ውጤት ማምጣቱ በትላንቱ ስብሰባ ላይ ተነስቷል። በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚው፤ በተያዘው በጀት ዓመቱ ሶስት ወራት በቁም እንስሳት ሽያጭ የተገኘው ገቢ በእቅድ ከተቀመጠው በላይ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ ወደ ውጭ ሀገራት ከላከችው 92 ሺህ ገደማ የቁም እንስሳት፤ 9.1 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን አቶ በረከት ተናግረዋል። ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ገቢ ሲነጻጸር ከሶስት እጥፍ በላይ ጭማሪ የታየበት እንደሆነ ጠቁመዋል። 

ሀገሪቱ በዚህ ወቅት ወደ ውጭ የላከችው የቁም እንስሳት በ2016 ዓ.ም. ከነበረው በቁጥር ከእጥፍ በላይ ቢሆንም፤ የዓለም አቀፍ ገበያው ዋጋ አነስተኛ መሆኑ የተገኘውን ገቢ ይበልጥ እንዳይጨምር እንዳደረገው አቶ በረከት አስረድተዋል። የዓለም አቀፍ ገበያው ተጽዕኖ፤ በቅባት እህሎች የወጪ ንግድ ላይም መስተዋሉን ስራ አስፈጻሚው አክለዋል። 

በዘንድሮ በጀት ዓመት ሶስት ወራት፤ ለዓለም አቀፍ ገበያ ከቀረቡ የቅባት እህሎች የተገኘው 39 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ የገቢ መጠን በእቅድ ከተቀመጠው 70 በመቶውን ብቻ ያሳካ እንደሆነ አቶ በረከት ገልጸዋል። በዚሁ ጊዜ ወደ ውጭ ሀገራት የተላከው የቅባት እህሎች መጠን፤ በእቅድ ከተያዘው 80 በመቶውን ብቻ የሸፈነ ነበር።  

በቅባት እህሎች የታየው ከእቅድ ያነሰ አፈጻጸም፤ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክትትል ከሚደረግባቸው ሌሎች ምርቶች ሁኔታ ጋር ተዳምሮ በዘርፉ ዝቅተኛ ገቢ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። ከእነዚህ ምርቶች ለማግኘት የታቀደው 180 ሚሊዮን ዶላር ነበር። የገቢ መጠኑ ለሩብ ዓመቱ ታቅዶ ከነበረው 87 በመቶው ብቻ ያሳካ ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ16.4 ሚሊዮን ዶላር የቀነሰ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጭ ከላከቻቸው የጫት እና የጥራጥሬ ምርቶች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ያነሰ ገቢ ብታገኝም፤ ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 1.508 ቢሊዮን ዶላር ማስመዘገቧ በትላንቱ ስብሰባ ልይ ይፋ ተደርጓል። ሀገሪቱ በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ለማግኘት ያቀደችው 5.2 ቢሊየን ዶላር ነው። 

በትላንቱ ስብሰባ ላይ የተገኙት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፤ ከእስካሁኑ አፈጻጸም በመነሳት በዘንድሮ በጀት ዓመት ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊገኝ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አቅም (potential) “20 እና 30 ቢሊዮን ዶላር እንጂ 3 እና 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠራበት” አለመሆኑን ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)