በሙሉጌታ በላይ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓለቲካ ፓርቲዎች ምዘገባ እና ለመሰረታዊ ሰነዶች ምዝገባ የሚጠይቀውን ክፍያ የጨመረው፤ “ድጎማን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ለማስቆም” መሆኑን ገለጸ። በክፍያ ተመኑ ላይ የተደረገው ማሻሻያ፤ “ወደፊት የሚመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን” የሚመለከት መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።
ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ይህን የገለጸው፤ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ይፋ ያደረገውን የክፍያ ተመን ማሻሻያ በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 16፤ 2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በማሻሻያው መሰረት፤ ቦርዱ ጊዜያዊ የዕውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት ጥያቄ ከሚያቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይጠይቅ የነበረውን የ100 ብር ክፍያ ወደ 15 ሺህ ብር አሳድጓል።
በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ የዕውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት ይከፍሉት የነበረው 200 ብርም፤ በአዲሱ የአገልግሎት ተመን ማሻሻያ ወደ 30 ሺህ ብር አሻቅቧል። ምዝገባቸውን በቦርዱ ያከናወኑ ፓርቲዎች፤ ለምርጫ ቦርድ የሚያቀርቧቸውን ሰነዶቻቸውን በሚያሻሽሉበት ወቅት የሚከፍሉት ተመንም ከ30 ብር ወደ አምስት ሺህ ብር ጨምሯል።

መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያከፋፈለው ገንዘብ መኖሩን ለጋዜጠኞች የተናገሩት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ “ይሄንን ጥቅም ብቻ ለማግኘት ብቻ እየታሰበ የሚሰራ ስራ በየጊዜው እየመጣ ነው” ሲሉ በምዝገባ ሂደት የሚሰተዋለውን ችግር አስረድተዋል። ምርጫ ቦርድ ወደፊት እንዲመጡ የሚፈልገው “ለፖለቲካ ስልጣን የሚታገሉ፣ የዲሞክራሲ አካሄዱን ማስፋት የሚችሉ ፓርቲዎችን” እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ተግባራዊ ያደረገው የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ “የድጎማ ፖለቲካ አካሄድን እና የድጎማ ፖለቲከኞችን፤ ገና ከጅምሩ ሁለት፣ ሶስቴ ማሰብ እንዳለባቸው ለማሳየት” ያለመ መሆኑንም ምክትል ሰብሳቢው ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ለምዘገባ እና በየጊዜው ለሚያደርጓቸው የሰነዶች ማሻሻያዎች፤ ለምርጫ ቦርድ የአገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለባቸው በአዋጅ ተደንግጓል።
በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የተመዘገቡ ፓርቲዎች፤ ከአባላቶቻቸው በመዋጮ ገንዘብ እንደሚሰብስቡ ያስታወሱት አቶ ውብሸት፤ ምርጫ ቦርድ ተግባራዊ ያደረገው የክፍያ ማሻሻያ በፓርቲዎች ላይ “ተጽዕኖ የሚፈጥር አይደለም” ባይ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአባላቶቻቸው መዋጮ በተጨማሪ ከኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ወይም ኢትዮጵያዊያን ከሚቆጣጠሯቸው ኩባንያዎች፤ በስጦታ አሊያም በእርዳታ ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉ በአዋጅ ተወስኖላቸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ ሰፍሯል። መንግስት ይህን የሚያደርገው “ህጋዊ ስራቸውን ለማከናወን እና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይችሉ ዘንድ” መሆኑም በአዋጁ ተመልክቷል።
ምርጫ ቦርድ የገንዘብ ድጋፉን ለፓለቲካ ፓርቲዎች ለማከፋፈል ከግምት ውስጥ ከሚያስገባቸው መስፈርቶች ውስጥ፤ ፓርቲዎች “በፌደራል እና በክልል ምክር ቤቶች ምርጫዎች የሚያገኙት የድምጽ ብዛት” የሚለው አንዱ ነው። ፓርቲዎች ለምርጫ ውድድር የሚያቀርቧቸው የሴት እና የአካል ጉዳተኛ እጩዎች ብዛት ሌላው በመስፈርትነት የተያዘ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸው የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች አባላት እና አመራሮች ብዛትም እንዲሁ በመስፈርትነት ተቀምጧል። ፓርቲዎች ከአባላት እና ደጋፊዎቻቸው የሚያገኙት የገቢ መጠን፤ ከመንግስት ለሚገኝ የገንዘብ ድጎማ በመስፈርትነት የሚታይ መሆኑም በአዋጅ ተደንግጓል።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ፤ አዋጁን በመንተራስ ባወጣው መመሪያ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመደጎም በዘንድሮ በጀት ዓመት 65 ሚሊዮን ብር ማከፋፈሉ በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። ይህን የገንዘብ ድጋፍ “ያለአግባብ ለመውሰድ” እና “ለመንጠቅ የሚያስቡ” የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አስታውቀዋል።
ይህን ለመከላከል፤ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች በሚሰጠው አገልግሎት ክፍያ ላይ የዋጋ ማሻሻያ መደረጉን ምክትል ሰብሳቢው አመልክተዋል። የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያው አነስተኛ የሚባል እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“በጣም ትንሽ ገንዘብ ነው። ግን ቢያንስ በቁምነገር የፖለቲካ ፓርቲ መስራቾች እንዲነጋገሩ ያደርጋል። አሁን መስራቾቹ ሳይነጋገሩ የሚቋቋም ነው የሚመስለው” ሲሉ አቶ ወብሸት አሁን ያለውን ችግር አስረድተዋል። “ነገ ከነገወዲያ የሚመጡ ፓርቲዎች፤ ‘መንግስት ገንዘብ መስጠት ጀምሯል፤ ስለዚህ እሱን እንዴት ነው የማገኘው’ ብለው ሊመጡ የሚሞክሩትን ለማስቆም [የተወሰነ ነው]” ሲሉም አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]