በምርጫ ቦርድ የታገዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ መሳተፋቸው ይቀጥላል ተባለ 

በናሆም አየለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ማናቸውንም ህጋዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ” ያገዳቸውን ፓርቲዎች፤ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ማሳተፉን እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ። ፓርቲዎቹ በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይም በተወካዮቻቸው በኩል እንዲሳተፉ እንደሚያደርግ ኮሚሽኑ አስታውቋል። 

ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው ከዛሬ ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚደረገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ አስመልክቶ፤ ትላንት እሁድ ጥቅምት 17፤ 2017 በወላይታ ሶዶ ከተማ በሰጠው መግለጫ ነው። በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ፤ በክልሉ ከሚገኙ 96 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ካሉት 11 ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ተናግረዋል። 

ተሳታፊዎቹ የወከሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች፣ እድሮች፣ አርሶ አደሮች እና የማህበረሰብ መሪዎችን መሆኑን ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል። ቁጥራቸው ሁለት ሺህ የሚጠጋው እነዚህ ተሳታፊዎች፤ በቀጣይ ሶስት ቀናት ለሀገር አቀፍ ጉባኤ የሚሆኑ የአጀንዳ ሃሳቦች ላይ ምክክር እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

ተወካዮቹ ከዚህ ምክክራቸው በኋላ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን፤ የክልሉን አጀንዳዎች የመለየት ስራን እንደሚሰሩ ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። የክልል ባለድርሻ አካላት የሚባሉት፤ የክልሉ የመንግስት አካላት፣ ማህበራትና ተቋማት፣ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በብሔራዊው ምርጫ ቦርድ እግድ የተጣለባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በምክክር ሂደቱ ላይ  ያላቸው ተሳትፎ እንደሚቀጥል ዶ/ር ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በጠቅላላ ጉባኤ”፣ “በኦዲት” እና “በሴት አባላት” ብዛት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ላይ “ጥሰት ፈጽመዋል” በሚል በምርጫ ቦርድ የታገዱ ፓርቲዎች ብዛት 11 ነው። 

ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ “ከማንኛው ህጋዊ እንቅስቃሴ” ታቅበው እንዲቆዩ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፤ ዶ/ር ዮናስ ግን እግዱ ፓርቲዎቹን በምክክሩ ሂደት ከመሳተፍ እና አጀንዳ ከመስጠት እንደማይከልክላቸው ገልጸዋል። ኮሚሽነሩ “ድርጅቶቹ በህጋዊነት የተመዘገቡ ሆነው፤ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ምክንያት” ከምክክሩ ሂደት ሊገለሉ አይገባም ባይ ናቸው። 

“እኛ እኮ መንግስት አሸባሪ ብሎ ለሰየመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጥሪ እያደረግን ነው። በአማራ ክልል ያሉ የፋኖ ታጣቂዎችን ኑ እንነጋገር እያልን ነው። በሀገር ውስጥ ካልተቻለ ውጪም ጭምር [ሄደን እንነጋገር] ብለን ጥሪ ማቅረብ ከጀመርን ሁለት አመት ሊሆነን ነው። ለእነርሱ ጥሪ የምናደርግ ከሆነ፤ እነዚህ ከእኛ ጋር አብረው እየሰሩ የነበሩን ሰዎች ‘በምክክሩ ሂደት አትሳተፉ’ ማለት አንችልም። በዚህ መሰረት ነው የምንሰራው” ሲሉ ዶ/ር ዮናስ የኮሚሽኑን አቋም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሎች በሚያደርገው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት፤ ለታገዱት ፓርቲዎች ጭምር ጥሪ እንደሚያቀርብም ኮሚሽነሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ድርጅቶቹ እግዱ ባይነሳላቸው እንኳን በሀገራዊ ጉባኤው ላይ በተወካዮቻቸው በኩል እንዲሳተፉ እንደሚደረጉም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ሂደት በዘጠኝ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አጠናቅቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ኮሚሽኑ በእነዚህ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉን በይፋ ያስጀመረው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር።

“እኛ እኮ መንግስት አሸባሪ ብሎ ለሰየመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጥሪ እያደረግን ነው። በአማራ ክልል ያሉ የፋኖ ታጣቂዎችን ኑ እንነጋገር እያልን ነው። በሀገር ውስጥ ካልተቻለ ውጪም ጭምር [ሄደን እንነጋገር] ብለን ጥሪ ማቅረብ ከጀመርን ሁለት አመት ሊሆነን ነው። ለእነርሱ ጥሪ የምናደርግ ከሆነ፤ እነዚህ ከእኛ ጋር አብረው እየሰሩ የነበሩን ሰዎች ‘በምክክሩ ሂደት አትሳተፉ’ ማለት አንችልም”

ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በዚህ መሰረት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሀረሪ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በአፋር  እና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮች ተካሄደዋል። ከእነዚህ የምክክር መድረኮች በኋላም፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ “ሊመከርባቸው ይገባሉ” የተባሉ አጀንዳዎችን ኮሚሽኑ ተረክቧል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ከተጀመረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በተጨማሪ በዚሁ ሳምንት መጨረሻ ተመሳሳይ መርሃ ግብር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ያካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። የተወካይ ምርጫ ካለቀባቸው ክልሎች ውስጥ፤ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ መቼ እንደሚካሄድ ያልታወቀው የኦሮሚያ ክልል ብቻ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)